April 20, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አመራሮችና አባላት አለም አቀፋዊ ተጽእኖዎችን መሻገር የሚያስችል የተሟላ ግንዛቤ በመያዝ ሀገራዊ ዕድገትን ዘላቂ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተጠቆመ።

የሸካ ዞን የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በወቅታዊው የአሜሪካ እስራኤልና የኢራን ጦርነት ስትራቴጂካዊ እንዲምታዎችና መሻገሪያ አቅጣጫዎች ላይ በሚያጠነጥን በፓርቲው በተዘጋጀ ሰነድ ዙሪያ ውይይት በጌጫ ከተማ አካሂደዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና በተከሰተው በወቅታዊው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ አለመረጋጋት ከጦርነቱ ተሳታፊ ሀገራት ባሻገር ሌሎች የዓለም ሀገራት በማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ተጽዕኖ እየደረሰባቸው ነው።

የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ግጭት ወደ ከፋ ደረጃ የተሸጋገረውና ዓለምን ያስደነገጠው መጠነ ሰፊ ጦርነት የጀመረው ፣አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን በኢራን ስትራቴጂካዊ ማዕከላት ላይ የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም የከፈቱትን ድንገተኛና የተቀናጀ ጥቃት ተከትሎ ነው።

ይህ ጦርነት በተለይም በማደግ ላይ በሚገኙ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ያይላል።

ኢትዮጵያ በተዘጋው የዓለም 20 በመቶ የንግድ እንቅስቃሴ የሚሳለጥበት ሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል 90 በመቶ ግብይት የሚትፈጽም ሲሆን በዚሁ ሳቢያ የተለያዩ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠች መሆኑን በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አብይ አንደሞ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በብልጽግና ፓርቲ መደመር እሳቤ  መሠረት ወቅታዊውን የመካከለኛው ምስራቅን ውጥረትን የባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መርህ በመከተል የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ማስከበር የሚያስችል መንገድ እየተከተለች መሆኑን አስረድተዋል።

በጦርነቱ ምክንያት የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ሀገር በቀል ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻዎችን ማስቀጠል፣ምርትና ምርታማነትን በማረጋገጥ ከተረጂነት ዕሳቤ መላቀቅ፣የግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማጠናከር ችግሩን ለመፍታት የተጀመረውን ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ያብራሩት ዶ/ር አብይ አንደሞ በተለይም በሸካ ዞን ይህን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ሰፊ ዕድሎች እንዳሉ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ጦርነቱ በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ላይ ልያሳድር የሚችለውን ተጽእኖዎችን ለመከላከል ፓርቲው እየሰራበት መሆኑንም ጨምሮ ተናግረዋል።

የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው ሀገራችን ፈተናዎችን በጽናት የመሻገርና ህልውናዋን የማስጠበቅ ልምድ እንዳላት በመጠቆም ይህን ልምድ ተጠቅሞ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት በባለፉት የለውጥ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የተሻገረችባቸውን ፈተናዎች በማሳያነት አንስተዋል።

በዞኑ የወቅቱ የፓርቲው አመራር አካላትና አባላት ወቅቱ የሚጠይቀውን ሀገራዊ አርበኝነት በልማት እንዲደግሙ በመግለጽ የተጀመሩ የዕድገት ተግባራት ላይ በመሳተፍ የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው አንስተዋል።

ወቅታዊዉ የፓርቲው አመራርና አባላት ውይይት እስከታችኛው አደረጃጀቶች ድረስ የሚቀጥል መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የሸካ ዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ዓለሙ ገልጸዋል። ዘገባው የዞኑ መ/ኮ ነው።