March 9, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤትነት ጥያቄ ለቀጣናዊ ሰላም ያለው ፋይዳ

ማሻ፤ የካቲት 30/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) ኢትዮጵያ በታሪካዊ አጋጣሚዎችና በሴራ ፖለቲካ ምክንያት አሁን የተገኘችበት የባሕር በር አልባነት ሁኔታ የብዙዎችን ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ሆኗል።

ይሁን እንጂ ታሪክ እንደሚመሰክረው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ ገናና ስምና ዝና የነበራት ከመሆኑም ባለፈ የቀጣናው የንግድና የፀጥታ ባለቤት የነበረች ታላቅ ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዘመናት እስከ ባብ ኤል-መንደብ ድረስ ባለው ሰፊ ግዛት የባሕር ወንበዴዎችንና አሸባሪዎችን ሥርዓት በማስያዝ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ነበራት። ለቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ዋስትና ያላት ወሳኝነትም ከፍተኛ ነው።

የቀይ ባሕር በር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንትና ከዓለም ጋር የምትገናኝበት ስትራቴጂካዊ መስመርም ነው።

በአሁኑ ወቅት በቀጣናው ጠንካራ የባሕር ኃይልና የፀጥታ ቁጥጥር ባለመኖሩ አካባቢው ለአሸባሪዎችና ለተለያዩ ስጋቶች ምቹ እየሆነ ይገኛል።

እንደ አል-ሸባብ ያሉ ቡድኖች አካባቢውን ለጥቃት ማሰናጃነት እየተጠቀሙበት ሲሆን፣ የኃያላን ሀገራት ወታደራዊ ፉክክርም ቀጣናውን የዲፕሎማሲ ፍጥጫ መድረክ አድርጎታል።

በቀጣናው የሚፈጠር ማንኛውም አለመረጋጋት በኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ላይ የዋጋ ንረትና የመርከቦች መዘግየት ያስከትላል።

ይህንን በመረዳት ብዙኃኑ የባሕር በር ጥያቄን ሀገራዊ አጀንዳ አድርገው ቢንቀሳቀሱም በግልባጩ የሀገርን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ አካላትም አልጠፉም።

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤትነት ጥያቄ የታሪክና የፍትሕ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገር ህልውና እና የቀጣናዊ ሰላም ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምን ለማስፈን የምታደርገው ጥረት ለጎረቤት ሀገራት አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

EBC