February 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

‘ቢስት ባር’ የቤንች ብሔር መነሻ በሆነው በሼይ ቤንች ወረዳ፣ ዣዥ ቀበሌ በድምቀት ተከበረ

ማሻ፤ ጥር 04/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ፀጋዬ ማሞ በዚሁ ወቅት፥ ኢትዮጵያ የበርካታ ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ቅርሶች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፤ እነዚህ ሀብቶች እንዲለሙ የመደመር መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፥ የጥንት አባቶቻችን ስልጣኔ ማሳያ የሆነው የቤንች ብሔር ዘመን መለወጫ ‘ቢስት ባር’ ከብሔሩ የዘመን አቆጣጠር ጋር በተያያዘ መንገድ የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ አዲስ እህል ሲደርስ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በጋራ ተካፍሎ በመቅመስ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ የምንሸጋገርበት፣ አዲስ ተስፋን የምንሰንቅበት ውብ ባህላዊ እሴታችን ነው ሲሉ አቶ ፍቅሬ ተናግረዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን፥ የቤንች ብሔር እንደ ማንኛውም ብሔር የራሱ የማንነት መገለጫዎች፣ ውብና ቱባ ባህሎች፣ ትውፊቶችና ክዋኔዎች ያሉት መሆኑን ገልጸዋል።

‘ቢስት ባር’ ከሩቅም ከቅርብም ያሉ የብሔሩ ተወላጆች በጋራ ተሰባስበው የሚያከብሩት፤ ለህጻናትና ወጣቶች ምክር የሚሰጡበት፤ ሰላም፣ አንድነትና አብሮነት በስፋት የሚንጸባረቅበት፤ የመደመር እሳቤ በተግባር የሚገለጽበት ታላቅ በዓል መሆኑን ጠቁመዋል።

የሼይ ቤንች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክፍሌ ጎበዜ በበኩላቸው፥ ‘ቢስት ባር’ እርስ በርስ መከባበርና አንድነት የሚገለፅበት በዓል ነው ብለው፤ ታሪካዊ ቦታ የሆነውን ዣዥ ቀበሌን ጠብቀው ላቆዩ አባቶች ምስጋና አቅርበዋል።

‘ቢስት ባር’ የክረምቱ ወራት ዝናብ፣ ጎርፍና ጭጋግ ተገፎ፣ ተፈጥሮ አዲስ ልብስ ለብሳ፣ መስኩ በአረንጓዴ አጊጦ፣ ወንዞች ኩልል ብለው ጠርተው፣ የአርሶ አደሩ እህል ደርሶ ወደ ጎተራ ሲገባ የቤንች ሕዝብ በጋራ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበትና የምሥራች ፍሬ የሚቀመስበት ውብ ባህል ነው።

‘ቢስት ባር’ በነገው ዕለትም በቤንች ሸኮ ዞን ዋና ከተማ ሚዛን አማን በቀድሞው አየር ሜዳ እንደሚከበር ኢቢሲ ዞኑን ጠቅሶ ያዘጋጀው ዘገባ ያመለክታል