February 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከቻይና አቻቸው ጋር ተወያዩ

ማሻ፣ ታህሳስ 30/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍኤም 103.8) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ጋር ተወያይተዋል።

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ጠንካራ እና በሁኔታዎች የማይቀየር ስትራቴጂካዊ አጋርነት አንስተዋል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የረጅም ጊዜ ወዳጅነት፣ ትብብር እና በጋራ መከባበር ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል።

ቻይና ለኢትዮጵያ ልማት እያደረገች ያለውን ድጋፍ በማድነቅ÷ ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ቻይና ያቀረበችውን የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና ልማት ኢኒሼቲቭ ተነሳሽነት ትኩረት በመስጠት   በቀጣናው ያሉ የደኅንነት፣ ልማትና አስተዳደር ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለውን ጠቀሜታም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የኢትዮ-ቻይና አጋርነትን በተለያዩ ባለብዙ መድረኮች ማለትም በአንድ ቀበቶና መንገድ ኢኒሼቲቭ፣ በቻይና-አፍሪካ ትብብር መድረክ፣ ብሪክስ-ፕላስ እና በተባበሩት መንግሥታት ማዕቀፎች ጨምሮ በትብብር ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።

ዋንግ ይ በበኩላቸው÷ ጉብኝታቸውን በፈረንጆቹ 2026 ወደ አፍሪካ ያደረጉት የመጀመሪያ መሆኑንና ኢትዮጵያ የመጀመሪያ መዳረሻቸው እንደሆነች አንስተዋል።

ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ዘላቂ አጋርነት እና ኢትዮጵያ ደግሞ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኗን ተናግረዋል።

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም ዓይነት አጋርነት በተለያዩ የትብብር ዘርፎች የበለጠ ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን የግንኙነት መድረኮች ላይ ስትራቴጂካዊ ቅንጅትን ለማጠናከርም ተስማምተዋል።

#FMC