February 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሸካ ዞን የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤት እያሳዩ መሆኑ ተገለጸ

ማሻ፣ ታህሳስ 24/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍኤም 103.8) ​በሸካ ዞን የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የታለሙ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት እያሳዩ መሆናቸው ተገለጸ።

የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሙኒኬሽን ፕሮግራም (JHU CCP) ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲያከናውናቸው የቆየውን የወጣቶች የክህሎት ሥልጠና ተግባራትን አስመልክቶ በቴፒ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግምገማ መድረክ አካሂዷል።

ፕሮጀክቱ በወጣቶች የክህሎት ግንባታ እና በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ያመጣው ውጤት የሚደነቅ መሆኑ ተገልጿል።

​በመድረኩ ላይ እንደቀረበው፣ ፕሮጀክቱ በዞኑ በቆየባቸው ሦስት ዓመታት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት የሚሆኑ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።

በክህሎት ግንባታ ረገድ 1 ሺህ 962 ወጣቶች የንግድ ሥራ ልማት ሥልጠና እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም ወጣቶቹ የራሳቸውን የሥራ ሃሳብ እንዲያመነጩና እንዲያስተዳድሩ አቅም ፈጥሮላቸዋል።

​ከሰለጠኑት ወጣቶች መካከል 432 የሚሆኑት (22 በመቶ) በደመወዝ፣ በራሳቸው ሥራ ወይም በብድር አማካኝነት ወደ ተጨባጭ የሥራ እንቅስቃሴ መግባታቸው ተመላክቷል።

የሥራ ማስጀመሪያ ካፒታል ችግርን ለመቅረፍም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ስርጭት የተከናወነ ሲሆን፣ በዚህም 370 ወጣቶች ተጠቃሚ ሆነዋል።

​የሸካ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምንተስኖት እንደሻው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ከመንግሥት መዋቅር ጋር ተቀናጅቶ በመሥራቱ በማህበረሰቡና በወጣቶች ዘንድ አዎንታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል።

ኃላፊው አክለውም ፕሮጀክቱ በተለይ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በክህሎት ሥልጠና ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራቱ የሚታይ ለውጥ መመዝገቡን አብራርተዋል።

በክልሉ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወ/ሮ እሊሊ ሆርዶፋ በበኩላቸው፣ ወጣቶች በክህሎት እንዲዳብሩና በአስተሳሰብ እንዲለወጡ የተከናወኑ ሥራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

​ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት የሥራ ዕድል ጠባቂ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ 530 የሚሆኑ ሥልጠና የወሰዱ ወጣቶች ሥራ ለመጀመር የብድር አቅርቦትን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

​የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የፋይናንስ አቅርቦቱ በፍጥነት እንዲመቻችና የብድር አሰባሰብ ሥርዓቱ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

በቀጣይም እነዚህን ወጣቶች ወደ ሥራ ለማስገባትና የተጀመሩ መልካም ተሞክሮዎችን በዘላቂነት ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።

#መ.ኮ.ጉ