ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሞሮኮ ወታደራዊ ልዑክ ጋር ተወያዩ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሞሮኮ ወታደራዊ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡ ፊልድ ማርሻሉ በሞሮኮው ምክትል ኢንስፔክተር ጀኔራል ስታፍ ሜጄር ጄኔራል አዚዝ ኢድሪሲ የሚመራ ወታደራዊ ልዑክን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ በውይይቱም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው ግንኙነቱ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ “አሁን የተዘጋውን በር ከፍተን አዲስ የግንኙነት መስመር ለመዘርጋት ውይይት እና ጉብኝት ማድረጉ መልካም ነገር ነውና እጅግ ደስተኞች ነን” ብለዋል፡፡ ሜጄር ጀኔራል አዚዝ እድሪሲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበርም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ ግዳጁን በብቃት መወጣት የሚችል ጠንካራ ወታደር ያላት ሀገር መሆኑን ተናግረዋል። ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት በአዲስ መልክ ለማደስ እና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ለመስራት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ልዑካን ቡድን በሞሮኮ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን በሚቀጥሉት ተከተታይ ቀናት የሞሮኮው ወታደራዊ ልዑክም በተቋሙ የተለያዩ ክፍሎች በመዘዋወር ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋል፡፡ከጉብኝቱ በኋላ የሚደረገው የሃሳብ ልውውጥ እና ውይይት ቀጣይ በሁለቱ ሀገራት መካካል ለሚደረገው ወታደራዊ ስምምነት እና የአፍሪካዊ ወንድማማችነት መንፈስ ታላቅ መሰረት ይጥላል ሲሉ ውይይቱን የተካፈሉት የመከላከያ ውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ መናገራቸውን የመከላከያ ሠራዊት የማህበራዊ የትስስር ገጽ ዋብ በማድረግ EBC ዘግቧል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሞሮኮ ወታደራዊ ልዑክ ጋር ተወያዩ

More Stories
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከ34 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል
በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ የበልግ የአረንጓዴ አሻራ በወረዳ ደረጃ የማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄዷል ።
በ2017 ዓ/ም አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ ከ399 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ ይካሄዳል፦ አቶ ማስረሻ በላቸው