አሜሪካ በደቡባዊ ኢራን በሚገኙ የኢራን የሚሳኤል ቤዞች እና ፈንጅ ሲቀብሩ ነበር ባለቻቸው ጀልባዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈፅማለች፡፡
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እንዳስታወቀው፥ ጥቃቱ በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ከጥቃት ለመከላከል የተደረገ እና የኢራንን ወታደራዊ ጫና ለመቀነስ ያለመ ነው።
በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ያለውን ጦርነት ለማቆም ስምምነት ለማድረግ ድርድር እየተደረገ መሆኑን የገለፀው የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ከስምምነት እስከሚደረስ የአሜሪካ ወታደራዊ ሃይል በሆርሙዝ ሰርጥ የጣለውን ክልከላ አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።
እስካሁን የአሜሪካን የአየር ጥቃት አስመልክቶ ኢራን የሰጠችው ይፋዊ ምላሽ የለም።
ይሁን እንጂ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በሆርሙዝ ሰርጥ አቅራቢያ በምትገኘው የባንደር አባስ ከተማ ፍንዳታ መሰማቱን እና የፍንዳታው ምንጭ እየተጣራ መሆኑን ዘግበዋል፡፡
ጥቃቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተካሄደ የሚገኘውን ድርድር ተፅዕኖ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አሁንም ድርድሩ እንደሚቀጥል ጠቁመው፥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በዛሬው እለት የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
More Stories
የሰው ልጅን አእምሮ ከኮምፒውተር ጋር የሚያገናኘው አስገራሚው የኢሎን ማስክ የሮቦት ቴክኖሎጂ
በ24 ሰዓት ውስጥ 25 መርከቦች በሆርሙዝ ሰርጥ አልፈዋል – ኢራን