የሠርግ ቀን ለአብዛኛው ሰው የአዲስ የሕይወት ምዕራፍ መጀመሪያ ቢሆንም፣ ለአንዳንዶች ግን የፈጠራ አቅማቸውን የሚያሳዩበት እና ስማቸውን በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ በደመቀ ቀለም የሚያሰፍሩበት ልዩ አጋጣሚ ነው።
በዚህ ዘገባ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ የሰፈሩ የብዙዎችን ስሜት የገዙ እና በዓለማችን የጋብቻ ታሪክ በልዩነታቸው የሚታወሱ አስገራሚ ሠርጎችን እንመለከታለን።
ጋብቻን በልዩ ድምቀት ለማክበር በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የሙሽራ ሚዜዎች ማሳተፍ አንዱ የፉክክር መድረክ ሆኗል።
በአሜሪካ ፍሎሪዳ የምትኖረው እና ቲና አክለስ የተባለችው ሙሽራ በሠርጓ ዕለት 168 ሚዜዎችን በአንድ መስመር በማሰለፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ መሆን ችላለች።
በሌላ በኩል፣ ሻርሊን ፒርሰን እና ሊዮ ዋትስ የተባሉ አውስትራሊያውያን ጥንዶች በጃፓን፣ ሂታ ከተማ ባዘጋጁት የሠርግ ሥነ-ሥርዓት 253 አበባ ያዥ (በታኝ) ልጃገረዶችን (Flower Girls) በማሳተፍ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግበዋል።
ጥንዶቹ ይህን ያደረጉት ሠርጋቸውን ለማድመቅ ብቻ ሳይሆን፣ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተጎዳችውን ከተማ ነዋሪዎች ልብ በደስታ ለመሙላት መሆኑ ተገልጿል።
የሠርግ ሥነ-ሥርዓታቸውን ልዩ ለማድረግ ጥልቁን የባሕር ዓለም እና የምድራችንን ዋሻዎች የመረጡ ጥንዶችም ጥቂት አይደሉም።
አድሪያን ዎተርስ እና ሱዛን ቤቴል የተባሉ ብሪታንያውያን ጥንዶች ከምድር ወለል በታች 137.16 ሜትር (450 ጫማ) ጥልቀት ባለው የዌልስ የድንጋይ ዋሻ ውስጥ በመግባት ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል።
በተመሳሳይ፣ ሂሮዩኪ ዮሺዳ የተባለ ጃፓናዊ እና ሳንድራ ስሚዝ የተባለች አሜሪካዊት ሙሽሮች በታይላንድ በሚገኝ 130 ሜትር ጥልቅ የውቅያኖስ ዋሻ ውስጥ ሠርጋቸውን አካሂደዋል።
ሌላኛው አስገራሚ ሠርግ ከወደ ሳይፕረስ ሲሆን፣ ማሪያ ፓራስኬቫ የተባለች ሙሽራ፣ ከሕፃንነቷ ጀምሮ የነበራትን የዓለም ክብረ ወሰን የመስበር ሕልም በሠርጓ ቀን እውን አድርጋለች።
ሙሽራዋ በሠርጓ ዕለት ያደረገችው የራስ መጋረጃ (Wedding Veil) ርዝመት 6 ሺህ 962.6 ሜትር (ወደ 23 ሺህ ጫማ ገደማ) የነበረ ሲሆን፣ ይህም 63 የእግር ኳስ ሜዳዎችን ማዳረስ የሚችል ነው።
ሕንዳውያኑ እህትማማቾች ሮሻን ሳሙኤል እና አንጀሊና ስካይ ደግሞ ለወላጆቻቸው የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ የጋብቻ ክብረ በዓል በጥቅሉ የ136.7 ሜትር ርዝመት ያላቸውን 9 ሺህ 400 አበቦች (Bouquet) አበርክተዋል።
የዕድሜ መግፋት ለፍቅር እንቅፋት እንደማይሆን ያሳዩት ሃሪ ስቲቨንስ በ103 ዓመታቸው የ84 ዓመቷን ቴልማ ሉካስን በማግባት የዓለማችን አንጋፋው ሙሽራ ሆነው ተመዝግበዋል።
በአንጻሩ ሚኒ ሙንሮ የተባለች አውስትራሊያዊት በ102 ዓመቷ የ83 ዓመቱን ዱድሊ ሪድን በማግባት አረጋዊቷ ሙሽራ ሆናለች።
የፍቅርን ጥፍጥና ደጋግመው ማጣጣም የፈለጉት አሜሪካውያኑ ሎረን ብሌየር እና ዴቪድ ሆፍ ብሌየር ደግሞ በተለያዩ የዓለም ሀገራትና ውብ ስፍራዎች ራሳቸውን 101 ጊዜ በጋብቻ በማስተሳሰር በዓለም ታሪክ ከፍተኛውን የጋብቻ ቃል-ኪዳን የማደስ ክብረወሰንን በጋራ ይዘውታል።
More Stories
በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰው ረቂቅ የሰላም ስምምነት ለሆርሙዝ ሰርጥ ደኅንነት…
የአመጋገብ ሥርዓታችንን ለመቀየር የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ተጠናክሮ ይቀጥላል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
የዲግሪ ሰርተፊኬት ህትመት በአንድ ማዕከል ብቻ ሊከናወን ነው