በሀገራችን ኢትዮጵያ የታየው ታሪካዊና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ካስገኛቸው ዘርፈ ብዙ ድሎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መመሥረት የለውጡ ጉዞ ህያውና ተጨባጭ ፍሬ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ አዲስ ክልላዊ አደረጃጀት ለዘመናት የታፈኑ የማንነትና የልማት ጥያቄዎችን ከመመለስ ባለፈ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የልማት መስኮች አመርቂና ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።
ከእነዚህም መካከል የዜጎችን መሠረታዊ የኑሮ ጥራት የሚወስነውና ለሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ እንደ ዋነኛ ተደርጎ የሚጠቀሰው የንጹህ መጠጥ ውኃ ዘርፍ፤ በክልሉ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እምርታዊ ለውጥ እየታየበት ያለ ዘርፍ መሆኑን የክልሉ ወኃና ማዕድን ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው ገልጸዋል።
ክልሉ ከተመሠረተበት ወዲህ በመንግስትና በሕዝብ የተቀናጀ አቅም እንዲሁም ከልማት አጋሮች ጋር በተደረገ ጥብቅ ትብብር በንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ረገድ መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን፤ ውጤትም መመዝገቡን የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።
በተለይም ግንባታቸው ተጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጠው ለረጅም ጊዜ ለሕዝብ ምሬትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምንጭ ሆነው የቆዩ የውኃ ተቋማትን ቅድሚያ በመስጠት የማጠናቀቅ ሥራ በልዩ ትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህ መሠረት ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ያሉት መዋቅሮች በጋራ ባደረጉት ርብርብ ባለፉት 5 ዓመታት ብቻ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ 632 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለሕዝብ አገልግሎት ማብቃት መቻሉን ኢንጂነር በየነ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የወደፊት የልማት ፍላጎትን ታሳቢ በማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት ለ27 ከተሞች የመጠጥ ውኃ ጥናትና ዲዛይን ተዘጋጅቶላቸዋል ብለዋል።
የተጠኑ ጥናቶች በጀት ሲገኝ ወዲያውኑ ወደ ግንባታ ምዕራፍ የሚሸጋገሩ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የክልሉን የውኃ ተደራሽነት ይበልጥ የሚያሰፋ እንደሚሆን አክለዋል።
በክልሉ እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች የክልሉን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ሽፋን ከነበረበት 32.7% ወደ 43% ከፍ ማድረግ የተቻለ ሲሆን የተጠቃሚ ህዝብ ቁጥርም ከነበረበት ከ1,287,547 ወደ 1,770,272 በማሳደግ የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት በተጨባጭ ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ 30 በላይ የሚሆኑ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ እንደሚገኙ ኢንጂነር በየኔ ጨምረው አንስተዋል።
ተገንብተው የተጠናቀቁ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓትም መዘርጋቱን አንስተው ለተቋማት አገልግሎት ዘላቂነቱ በየደረጃው ያሉ የባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
More Stories
ዓለምን እያነጋገረ ያለው ‘ሀንታ ቫይረስ’
ለወረርሽኝና ለድንገተኛ አደጋ የማይበገር የጤና ስርዓት ለመዘርጋት የጤና ዘርፍ አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርምን በሙሉ አቅም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።
የሙዝ የጤና ጥቅሞች 🤍