May 19, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ዓለምን እያነጋገረ ያለው ‘ሀንታ ቫይረስ’

በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ በሚጓዝ አንድ የቱሪስት መርከብ ላይ የ‘ሀንታ ቫይረስ’ ወረርሽኝ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የቫይረሱን ስርጭት ተከትሎ፣ ድርጅቱ እና የተለያዩ ሀገራት የጤና ተቋማት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ እያሳሰቡ ይገኛሉ።

በአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (CDC) መረጃ መሰረት ሀንታ ቫይረስ በዋነኝነት የሚተላለፈው የቫይረሱ ተሸካሚ የሆኑ አይጦች ሽንት፣ እዳሪ ወይም ምራቅ ወደ አየር ሲቀላቀል እና ሰዎች ያንን አየር ወደ ውስጥ ሲተነፍሱ ነው።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ እና የሞት መጠኑም ስጋት ላይ የሚጥል መሆኑ ተገልጿል።

ቫይረሱ ረዥም ጭራ ባላቸው አይጦች ፈሳሾች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ከባድ የመተንፈሻ አካላት ችግር (Hantavirus Pulmonary Syndrome) ሊያስከትል የሚችል የቫይረስ ዓይነት ነው።

በዚህም ምክንያት እስካሁን የሦስት ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በላቦራቶሪ የተረጋገጡ አምስት ታማሚዎች ተገኝተዋል፤ ሌሎች ስምንት የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ደግሞ በክትትል ስር ይገኛሉ።

ሟቾቹ ለቀናት የቆየ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ የጡንቻ ሕመም እና ሳምባ በፈሳሽ በመሞላቱ ምክንያት የመተንፈስ ችግር ታይቶባቸው እንደነበር ተገልጿል።

ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ የሀንታ ቫይረስ ዝርያዎች ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፉ ቢሆንም፣ የዓለም ጤና ድርጅት ጥንቃቄን ለማስቀደም ሲል ቫይረሱ የታየባቸው እና ከታማሚዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ለ45 ቀናት ያህል በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ አድርጓል።

ይህም ረጅም ጊዜ የተመረጠው ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ተደብቆ የሚቆይበትን ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ነው።

ሀንታ ቫይረስ ለሞት የመዳረግ ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ማንኛውም ሰው መሰል ምልክቶች ሲታዩበት በአቅራቢያው ወዳለ የጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል።

ሁኔታው በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ዓለም አቀፍ ተጓዦች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።