በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰውና የዓለምን ኢኮኖሚ እያናጋ የሚገኘው ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊቆም እንደሚችል የሚጠቁሙ አዳዲስ ተስፋ ሰጪ መረጃዎች ተሰምተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት በሰጡት መግለጫ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ የምታደርገውን ጥቃት ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ልታቆም እንደምትችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ጦርነቱን ለማቆም የግድ የሰላም ስምምነት መፈረም ላያስፈልግ እንደሚችል በመግለጽ ግጭቱ በቅርቡ ሊያበቃ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ በጣም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምናልባትም በሁለት ወይም በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ከአካባቢው እንደምትወጣም ጠቁመዋል።
ኢራን ለረጅም ጊዜ ወደ ኒውክሌር መሣሪያ ማበልጸግ የማትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷን ስናረጋግጥ አካባቢውን ለቀን እንወጣለን ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ይህ የትራምፕ መግለጫ የተሰማው በአሜሪካ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን ተከትሎ በፕሬዝዳንቱ ላይ የሚሰነዘረው የውስጥ ግፊት በበረታበት ወቅት ነው ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።
ምንም እንኳን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ድርድር እየተደረገ አለመሆኑን ቢገልጹም በሁለቱ ሀገራት መካከል በተዘዋዋሪ የሚደረጉ የመልዕክት ልውውጦች ግን ለሰላም ጥረቱ በር ከፋች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመላክቷል።
ኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴዋ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ እንደሆነና የኒውክሌር መሣሪያ ለማምረት ፈልጋ እንደማታውቅ በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷ ይታወሳል።
More Stories
ኢራን የቻይናው ፕሬዚዳንት ያቀረቡትን ባለ አራት ነጥብ የሰላም የውሳኔ ሐሳብ እንደምትደግፍ ገለጸች
የኢትዮጵያ እና የተመድ የ80 ዓመታት ታሪካዊ ቁርኝት
ለ7ኛዉ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የብልፅግና ፓርቲ ይምረጡኝ ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ በአንድራቻ ወረዳ ጌጫ ከተማ ተካሂደዋል ።