በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስምንት ዐሥርተ ዓመታት ጉዞ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ በጋራ ደኅንነት፣ በሰላም እና በልማት ፅኑ አቋም ይዛ በዓለም አቀፍ መድረክ ደማቅ አሻራዋን አኑራለች።
ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሻገረው የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ጉዞ ተመድ የተመሠረተበትን በዓል ሲያከብር፣ የድርጅቱ ቀዳሚ መሥራች እና ንቁ ተሳታፊ የሆነችው ሀገራችን በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፣ በሰላም ማስከበር እና በልማት ትብብር ረገድ ያሳለፈቻቸው ዓመታት በክብር ይወሳሉ።
እ.አ.አ በ1945 ተመድ ሲመሠረት፣ ኢትዮጵያ ቻርተሩን ከፈረሙ 51 ቀዳሚ መሥራች ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች።
ይህም በወቅቱ በቀኝ ግዛት ሥር ለነበሩት በርካታ የአፍሪካ እና የእስያ ሀገራት ትልቅ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ታሪካዊ ክስተት ነበር።
ታዲያ ይህ ግንኙነት ለሌሎች ሀገራት ከተስፋነት በዘለለ፣ ላለፉት 80 ዓመታት ጠንካራ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ኖሮት ቀጥሏል።
በተባበሩት መንግሥታት የታሪክ ድርሳን ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ጎልቶ ከሚነሳባቸው ተግባራት ቀዳሚው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ነው።
ከ1950ዎቹ የኮሪያ ጦርነት ጀምሮ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በዳርፉር እንዲሁም በቅርብ ጊዜያት በአብዬ እና በደቡብ ሱዳን የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገራት ሰላም ዘብ በመቆም ግንባር ቀደም ሚናዋን ተወጥታለች።
ኢትዮጵያ ለተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በርካታ የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በመላክ ከግንባር ቀደምት ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ ሆና ቀጥላለች፡፡ ይህም ለዓለም ሰላም እና መረጋጋት ያላትን ፅኑ አቋም በተግባር ያሳየችበት ነው።
አዲስ አበባ የድርጅቱ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) እና የሌሎች በርካታ የተመድ ኤጀንሲዎች መቀመጫ መሆኗ የኢትዮጵያና የተባበሩት መንግሥታት ግንኙነት ሌላው ትልቅ መገለጫ ነው።
እ.አ.አ በ1958 የተመሰረተው ይህ ኮሚሽን አዲስ አበባን ከኒውዮርክ እና ከጄኔቫ በመቀጠል የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል።
ይህ ትብብር ኢትዮጵያ በአህጉራዊ የልማት አጀንዳዎች እና በኢኮኖሚ ትሥሥር ዙሪያ ያላትን ሚና በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል።
ተመድ 80ኛ ዓመቱን ሲያከብር ኢትዮጵያ የድርጅቱ ቻርተር እንዲከበር፣ የአፍሪካ ድምፅ በፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ሰጪነት ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዲኖረው እና በዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ዙሪያ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ያላትን አጋርነት እያጠናከረች ትገኛለች።
የኢትዮጵያና የተባበሩት መንግሥታት የ80 ዓመታት ጉዞ፣ ለቀጣዩ ትውልድም በጠንካራ መሠረት ላይ ተገንብቶ ዘላቂ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንደሚቀጥል ይታመናል።
More Stories
ኢራን የቻይናው ፕሬዚዳንት ያቀረቡትን ባለ አራት ነጥብ የሰላም የውሳኔ ሐሳብ እንደምትደግፍ ገለጸች
ወደ ልዩ አጋርነት ያደገው የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ወዳጅነት
ለ7ኛዉ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የብልፅግና ፓርቲ ይምረጡኝ ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ በአንድራቻ ወረዳ ጌጫ ከተማ ተካሂደዋል ።