May 13, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ወደ ልዩ አጋርነት ያደገው የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ወዳጅነት

የ129 ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ታሪክ ያላቸው ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ሁሉን አቀፍ አጋርነት እና ትብብራቸው ወደ ልዩ አጋርነት አድጓል፡፡

የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ወዳጅነት ትብብር ከለውጡ ወዲህ በጉብኝት ልውውጦች እና የሁለትዮሽ ውይይቶች ይበልጥ እየጠነከረ መጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም በአውሮፓ ሀገራት የስራ ጉብኝት ሲያደርጉ የመጀመሪያዋ መዳረሻቸው ፈረንሳይ ነበረች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በዓለም አቀፍ መድረክ አንድ በሚያደርጓቸው አጀንዳዎች፣ በጸረ ሸብርና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ይታወሳል፡፡

ከዚህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የፈረንሳይ ጉብኝት ከአምስት ወራት በኋላ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራርመዋል።

ከስምምነቶቹ መካከል ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ እድሳት የሙያና የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግበት ማዕቀፍ የሚጠቀስ ሲሆን ማክሮን በወቅቱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአራት ዓመታት በኋላ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በፈረንሳይ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ትስስር እየጎለበተ መጥቷል።

በርካታ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በንግድ ልውውጥ ረገድ ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡና ወደ ፈረንሳይ ስትልክ ፈረንሳይ በበኩሏ፤ የትራንስፖርት ቁሳቁስና የህክምና መገልገያ መሳሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በዋናነት ትልካለች።

በሲቪል አቪዬሽን፣ በአየር ትራንስፖርት እና መሰረተ ልማት ዘርፎች ትብብራቸውን ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ያደረጉት ሀገራቱ፤ በዘርፎቹ በትብብር እየሰሩ ይገኛል።