May 13, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ኢራን የቻይናው ፕሬዚዳንት ያቀረቡትን ባለ አራት ነጥብ የሰላም የውሳኔ ሐሳብ እንደምትደግፍ ገለጸች

ቴህራን የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ለመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ያቀረቡትን ባለ አራት ነጥብ የውሳኔ ሐሳብ የምትደግፍ መሆኗን አስታውቃለች ሲሉ በቻይና የኢራን አምባሳደር አብዶልሬዛ ራህማኒ ፋዝሊ ገለጹ።

የኢራን ድጋፍ በፋርስ ባህረ ሰላጤ ቀጣና ዘላቂ ደኅንነትን ለማስፈን እና የጋራ ልማትን ለማምጣት ያለመ መሆኑን አምባሳደሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸዋል።

ይህ ጉዳይ በሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት ወቅትም ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል።

ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላምን እና መረጋጋትን ለማስፈን የሚያስችለውን ይህንን ባለ አራት ነጥብ ዕቅድ ያቀረቡት ቀደም ሲል ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ፕሬዚዳንት ዛይድ አል ናህያን ጋር በቤጂንግ ባደረጉት ውይይት ወቅት እንደነበር ተገልጿል።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ያቀረቡት ባለአራት ነጥቡ የሰላም የውሳኔ ሐሳብ፦

ለሰላማዊ አብሮነት ቁርጠኝነት ማሳየት፦ ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለፋርስ ባህረ ሰላጤ ቀጣና “የጋራ፣ አስተማማኝ፣ በትብብር ላይ የተመሠረተ እና ዘላቂ” የሆነ የደኅንነት መዋቅር እንዲገነባ ማበረታታት፤

ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ማክበር፦ የቀጣናው ሀገራት ሉዓላዊነት፣ ደኅንነት እና የግዛት አንድነት ሙሉ በሙሉ እንዲከበር ማድረግ፤ እንዲሁም የግለሰቦችን፣ የተቋማትን እና የመሠረተ ልማቶችን ደኅንነት በተሟላ ሁኔታ ማረጋገጥ።

ዓለም አቀፍ የሕግ የበላይነትን ማክበር፦ የዓለም ሥርዓት ሕግ ወደሌለበት እና ኃያላን ደካሞችን ወደሚበሉበት (Law of the jungle) ሥርዓት እንዳይቀየር፣ የዓለም አቀፍ ሕግጋትን ተፈጻሚነት እና የበላይነትን ማስጠበቅ እንዲሁም

በልማት እና በደኅንነት መካከል ቅንጅት መፍጠር፦ ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለፋርስ ባህረ ሰላጤ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ብልጽግና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሁሉም ወገኖች በትብብር እንዲሠሩ ማበረታታት የሚሉ እንደሆኑ ተዘግቧል።

#EBC