May 6, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሸካ ዞን ቴፒ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው በክልሉ የመጀመሪያ የሆነው የግል ጤና ጣቢያ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በተገኙበት ተመረቀ።

ማሻ ፣ የሚያዝያ 26፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) በምረቃው ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ በከተማው የተገነባው ይህ ጤና ጣቢያ የአካባቢው ማህበረሰብ የጤና አገልግሎት ፍላጎትን ከማሟላት ረገድ ሚናው የጎላ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

አምራችና ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር እንደ ሀገር የተያዘውን ህልም እውን ለማድረግ የጤናው ዘርፍ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀው ይህንንም ከማረጋገጥ አኳያ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የግሉንም ተቋም ደረጃ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደዚህ አይነት ትላልቅ ኢንቨስትመንት አስፈላጊ መሆኑን መንግስታችን ስለሚያምን በሁሉም ዘርፍ ለመሰማራት የሚፈልጉ አልሚ ባለሀብቶች በዞኑ መጥተው እንዲያለሙና መንግስትም ተገቢውን ድጋፍ በተጠየቀው ሁሉ ያደርጋል ለዚህም በሁሉም የዞኑ የመንግስት መዋቅር በተቀናጀ መልኩ ይሰራል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሩ ወዬሳ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት ተቋሙን በመደገፍና አስፈላጊውን ስልጠናና ክትትል ከማድረግ አንፃር በትኩረት እንደሚሠራ ገልፀው ከመንግስት ተቋማት ጋር የማስተሳሰር ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የቴፒ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ወንድሙ ግርማ ባስተላለፉት መልዕክት የከተማውን ህብረተሰብ የጤና አገልግሎት አቅርቦት ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ተቋም እንደሚሆንና ከተማዋ በሚታደርገው የደረጃ ለውጥ ስራ በማህበራዊ ዘርፍ መስፈርት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አስታውሰዋል።

የጤና ጣቢያው ባለቤት ይታያል ተካ ተቋሙን ሲያስጎበኙ እንደተናገሩት በአጠቃላይ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተገነባና ከ25 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች በስሩ እንዳሉት ተናግረው ከአገልግሎት አንፃርም ቀላል ምርመራ፣የእናቶችና ህፃናት ጤና እንክብካቤ፣ ቅድመና ድህረ ወሊድ ክትትል፣የማዋለድ አገልግሎት፣የቀዶ ህክምናን ጨምሮ ሁሉንም ምርመራና ህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በቀጣይም አገልግሎቱን በማስፋትና በማሳደግ ወደ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለማሳደግ እቅድ እንዳላቸው የጠቆሙት ባለሃብቱ አስፈላጊውን ድጋፍ መንግስት እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።