August 19, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በወረዳው የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲጎለብት አደረጃጀቶችን ማጠናከር ላይ ትኩረት ማድረጉን በብልጽግና ፓርቲ የአንድራቻ ወረዳ የወጣቶች ክንፍ ጽ/ቤት ገለጸ

ጽህፈት ቤቱ “ጠንካራ የወጣቶች አደረጃጀት ፤ሀገረ መንግስት ግንባታ “በሚል መሪ ቃል የ2018 በጀት ዓመት የማጠቃለያ መድረክና የቀጣይ 2019 ዓ/ም ተግባራት ዕቅድ ዙሪያ የምክክር መድረክ በጌጫ ከተማ አካሂዷል ።

የመድረኩ ዓላማ በዋናነት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በወጣቶች አደረጃጀት ዙሪያ የታዩ ጠንካራ ተግባራትን በማስቀጠል ድክመቶችን በማረም ሁለንተናዊ የወጣቶች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማስቻል እንደሆነ በወረዳው የወጣቶች ክንፍ ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ተሻገር መኮንን ተናግረዋል ።

የወጣቶች ተሳትፎ በሁሉም ዘርፎች እንዲያይል የተለያዩ አደረጃጀቶችን ማጠናከር ትኩረት ተደርጓል ያሉት ኃላፊው ይህም እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ይቀጥላል ብለዋል።

በተለይም በስራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ስለመሆኑም ገልጸዋል ።

በክረምት ወራት ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ በማሳተፍ ተግባሩ በወጣቶች ዘንድ ባህል ሆኖ እንዲቀጥልና ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የሚቀጥሉ ናቸውም ብለዋል።

ወቅቱን የጠበቀ ሪፖርት ማቅረብ ፣የመዋጮ አከፋፈል ስርዓትን ማሻሻል ፣የአባላት ቁጥር መጨመርና በተለያዩ ቀበሌዎች በሚከወኑ የልማት ተግባራት ላይ መሳተፍ በቀጣይ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባም አቶ ተሻገር አሳስበዋል ።

በወረዳው በብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊው አቶ አመነ አሰፋ በበኩላቸው ወጣቶች በተለይም ሰባተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በሰላማዊ ሂደት እንዲጠናቀቅና ምርጫው በብልጽግና ፓርቲ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ያደረጉት ተጋድሎ የሚመሰገን መሆኑን አንስተዋል ።

የወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በወረዳው ከፍተኛ ቁጥር የያዘ መሆኑን የተናገሩት አቶ አመነ በቀጣይ በወረዳው ተተኪ በመሆናቸው በሁሉም ዘርፎች ወጣቶችን ለማብቃት መንግስት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።

የተለያዩ ወጣት አደረጃጀት ዘርፍ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ትኩረት በማድረግ በወጣቶች ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት እልባት እንዲሰጡ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው በወረዳው በየቦታው ያደሩ የወጣቶች ተጠቃሚነት ጥያቄን መፍትሔ ማስገኘት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለወጣቶች ተጠቃሚነት በጋራ መቀናጀት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ተሳታፊዎቹ በተያዘው በጀት ዓመት የተሻለ ስራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የተናገሩት ።