July 15, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

መሰረታዊና ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር መፍታት ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል-አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ገለጹ፡፡

የኮሚሽኑ ቃል-አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለጋዜጣ ፕላስ እንደተናገሩት፣ መሰረታዊ ችግሮችን በሀገራዊ ምክክር መፍታት ለሀገሪቱ አዲስ ምዕራፍ ነው። ሀገራዊ ምክክር ብዙ ሂደቶችን አልፎ የምክክር መድረክ መፈጠሩ ለዚች ሀገር ታሪካዊ ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ መምከር ከጀመረች አራት ዓመታትና ጥቂት ወራት መቆጠሩን አስታውሰው፤ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ኢትዮጵያ በምክክር ሂደት ላይ መሆኗንና ወደፊትም እየመከረች መቀጠል እንዳለባት ገልጸዋል፡፡

ሐምሌ 8 የሚጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያውያን እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ተመካክረው መግባባት ላይ የሚደርሱበት ይሆናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እየተዋጋች፣ እየተጋጨች፣ ነገሮች እየተወሳሰቡ መቀጠል እንደሌለባት በመግለጽ፤ ልዩነቶችና አለመግባባት ዛሬም አለ፣ ወደፊትም ይኖራል። ችግሮች የሚፈቱበት መንገድ ግን በምክክርና ሰለጠነ ዕሳቤ መሆን አለበት ብለዋል።

በመሣሪያ ሰው እያለቀ፣ ንብረት እየወደመ፣ ሀገር ወደኋላ እየተመለሰና ማኅበራዊ ግንኙነቶች እየሻከሩ መቀጠል እንደሌለበት ጠቅሰው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮች የሚፈቱበት መሣሪያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጋዜጣ_ፕላስ