March 26, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በ48 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ወጪ 500 ሺህ ዘመናዊ ቆጣሪዎችን ለመግጠም እየተሰራ ነው

በ48 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ወጪ በሀገር አቀፍ ደረጃ 500 ሺህ ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን ለነባርና አዲስ ደንበኞቹ ለመግጠም የሚያስችል ፕሮጀክት እየተተገበረ ነው ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር እንዳሉት÷በፕሮጀክቱ 125 ሺህ ስማርት ሶስት ፌዝ፣ 25 ሺህ ስማርት ነጠላ ፌዝና 350 ሺህ ኦፍላይን ነጠላ ፌዝ ዘመናዊ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን ለመግጠም እየተሰራ ይገኛል፡፡

እስካሁን በተከናወነው ሥራ 60 ሺህ 457 ነጠላ ፌዝ ቆጣሪዎችን እስከ 7 ነጥብ 5 ኪሎ ዋት ድረስ ኃይል ለሚጠቀሙ ለመኖሪያና ለንግድ ደንበኞች መገጠማቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም 7 ሺህ 13 ባለ ሦስት ፌዝ ቆጣሪዎች ከ8 እስከ 24 ኪሎ ዋት ድረስ ኃይል ለሚጠቀሙ ለመኖሪያ፣ ለንግድና ለአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ተገጥመው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ ዘመናዊ ቆጣሪዎች የቅድመ ክፍያ ደንበኞች ወደ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ሳይሄዱ የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም ቶክን ቁጥር በመግዛት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሞሉ የሚያስችሉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በአሁን ወቅት ከ67 ሺህ በላይ ደንበኞች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በኢትዮ ቴሌኮምና በአዋሽ ባንክ የሞባይል አፕሊኬሽኖች ሳምንቱን ሙሉ ቤታቸው ሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት እንዲችሉ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

ቀድሞ የነበሩ የቅድመ ክፍያ ካርድ መጥፋት፣ የካርድ መበላሸት፣ የኔትወርክ መቆራረጥ እንዲሁም ቆጣሪው ላይ ብር አልገባልኝም የሚሉትን ችግሮች እንደሚያስቀርም አቶ አንዋር ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡