May 6, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ቲክቶክ፣ ስናፕቻት፣ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ተከሰሱ

14 የካናዳ ትምህርት ቤቶች በ4 ግዙፍ የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ላይ ክስ መስርተው የ8 ቢሊዮን ዶላር ከሳ ጠይቀዋል።ክሱ የተመሰረተባቸው ኩባንያዎች ቲክቶክ፣ ስናፕቻት፣ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ናቸው።የ14ቱ ትምህርት ቤቶች ቦርዶች አራቱን ኩባንያዎች የከሰሷቸው የተማሪዎችን የአዕምሮ ጤና ጎድተዋል በሚል መሆኑን ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል።ቦርዶቹ በኩባንያዎቹ ላይ በፍርድ ቤት ክስ ከመሰረቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት በተጠቀሱት ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚንሸራሸሩ ሀሳቦች “የህጻናትን አስተሳሰብ፣ ባህርይ እና የትምህርት አቀባበል ቀይረዋል” ብለዋል።በኦንታርዮ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን የሚወክሉት የ14ቱ ትምህርት ቤቶች ቦርዶች በተማሪዎች የአዕምሮ ጤና እና ደህንነት ላይ የደረሰው ጉዳት ካሳ ያስፈልገዋል ብለዋል።ሁሉም ቦርዶች ከአራቱ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከካሳ ክፍያው በተጨማሪ በቀጣይ በተማሪዎች ላይ የሚሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችሉ ትላልቅ ለውጦችን እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል። ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው የሜታ ኩባንያ ቃል አቀባይ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም “የታዳጊዎችን ደህንነት የማይፃረሩ፣ ይልቁንም አጋዥ የሆኑ፣ የወላጆችንም ፍላጎት የሚያከብሩ ተሞክሮዎችን የሚያጋሩ ናቸው” ብለዋል።ይሁን እንጂ ይህ የኩባንያው ምላሽ በቦርዶቹ ተቀባይነት አላገኝም። ልጆቻችን አዕምሯቸው፣ ውሏቸው እና የትምህርት አቀባበላቸው የተቀየረው እነዚህ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከተስፋፉ በኋላ ነው ብለው ያምናሉ።ከካናዳ በተጨማሪ ወደ 500 የሚጠጉ የአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ቦርዶችም በኩባንያዎቹ ላይ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል ሲል የዘገበው ቲአርቲ ወርልድ ነው።

Al-Ain