የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት ተከብሯል።
በዓሉን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንቱ፣ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት አንድ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን የሕዝብ ጤና ጥበቃና ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ የጤና ሥርዓታችን የጀርባ አጥንት ሆኖ ማገልገሉን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ጉለሌ አነስተኛ የክሊኒካል ላቦራቶሪ ሆኖ የተጀመረው ይህ ተቋም፣ በዶክተር ቶማስ ላምቢ ፈር ቀዳጅ ሥራዎች በመነሳሳት በርካታ ተቋማዊ ሽግግሮችን በማድረግ ዛሬ ላይ ለሚገኘው ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ኢንስቲትዩት ደረጃ መድረሱን በበዓሉ ላይ ተወስቷል።
ኢንስቲትዩቱ በአንድ ክፍለ ዘመን የአገልግሎት ዘመኑ፣ ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን ወደ ተግባራዊ ብሔራዊ የጤና ፖሊሲዎች በመተርጎም ረገድ የነበረው ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደነበር ተገልጿል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፣ ተቋሙ በሕብረተሰብ ጤና ስጋቶች፣ ወረርሽኞችና በሽታዎች በሚከሰቱበት ወቅት ወቅታዊና ሕይወት አድን ምላሾችን በመስጠት ሁልጊዜም በግንባር ቀደምትነት እንደሚቆም አስረድተዋል።
በተለይም እንደ ኮቪድ-19፣ የዝንጀሮ ፈንጣጣና የማርበርግ ቫይረስ ያሉ ወረርሽኞችን ቀድሞ በመለየትና በአፋጣኝ በመቆጣጠር ረገድ ኢንስቲትዩቱ ያከናወናቸው ተግባራት ለዜጎች ጤና ጥበቃ ያደረጉት አበርክቶ ዘመን የማይሽረው መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የላቦራቶሪ ምርመራ ሥርዓት በመዘርጋትና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ወረርሽኞችን አስቀድሞ የመተንበይ አቅም እየገነባ ይገኛል።
በ2018 በጀት ዓመት ብቻ ከ7 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ላይ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን አስመልክቶ የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች መከናወናቸው የኢንስቲትዩቱን አቅም ያሳያል።
ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ በሚገኘው በዚህ በዓል፣ ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ በምሥራቅ አፍሪካ የሕዝብ ጤና ምርምርና ስልጠና ግንባር ቀደም ተቋም ለመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
More Stories
አሜሪካ የመርከቦችን እንቅስቃሴ እያወኩ ነው ባለቻቸው የኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ አዲስ ጥቃት ፈጸመች፡፡
አፍሪካ በጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት የምታነሳው ጥያቄ ፍትሃዊ ነው – የአዘርባጃን ፕሬዚዳንት
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በመከላከያ ጠቅላይ መመሪያ ግቢ የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በይፋ አሥጀምረዋል።