April 14, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

አትሌቲኮ ማድሪድ ከ ባርሴሎና፣ ሊቨርፑል ከፒ ኤስ ጂ

የዛሬው የአትሌቲኮ ማድሪድ እና የባርሴሎና ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በዚህ የውድድር ዓመት ብቻ ለ6ኛ ጊዜ የሚገናኙበት ነው። ባለፈው ሳምንት ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በካምፕ ኑ ባርሴሎናን ያሸነፈው አትሌቲኮ ማድሪድ፣ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሜዳው የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል።

ምንም እንኳን አትሌቲኮ የሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታውን 2 ለ 0 ቢያሸንፍም፣ የባርሴሎናው ኮከብ ላሚን ያማል በሰጠው አስተያየት “ጨዋታው ገና አልተጠናቀቀም” ብሏል። በመድረኩ ባርሴሎና ከ4 ለ 0 ሽንፈት ተነስቶ ፒኤስጂን 6 ለ 1 ያሸነፈበትን እና የማይታመነውን ውጤት የቀለበሰበትን ታሪክ ያስታወሰው የ18 ዓመቱ ያማል፤ “እኛም ይህንን ለማድረግ ወደ ዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ እናመራለን” ሲል ተናግሯል። የቡድኑ አሰልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ በበኩላቸው ይህንን ውጤት ቀይሮ ማለፍ ለባርሴሎና ተዓምር ሊሆን እንደማይችል በመጥቀስ፣ ለመልሱ ጨዋታ በሚገባ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ ምሽት የሚገናኙት በአጠቃላይ ለ252ኛ ጊዜ ሲሆን፣ የካታላኑ ክለብ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት የዲዬጎ ሲሚዮኒን የጠነከረ የመከላከል ግድግዳ መስበር ይኖርበታል። የዚህ ዓመቱ አትሌቲኮ ማድሪድ ምንም እንኳን በሊጉ ጥሩ ግስጋሴ ላይ ባይገኝም፣ በሌሎች የዋንጫ ፉክክሮች ግን ጠንካራ መሆኑን እያሳየ ይገኛል። በስፔን ኮፓ ዴል ሬይ ባርሴሎናን አሸንፎ ለፍጻሜ መድረሱ ይታወሳል። በዛሬው ጨዋታ በአትሌቲኮ በኩል ማርክ ቡቢል በቅጣት የማይሰለፍ ሲሆን፤ ጂሚኔዝ፣ ፓብሎ ባሪዮስ እና ዴቪድ ሃንኮ በጉዳት ምክንያት የመሰለፋቸው ነገር አልተረጋገጠም።

በሌላ የሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ፣ በመጀመሪያው ጨዋታ 2 ለ 0 ተሸንፎ የተመለሰው ሊቨርፑል በሜዳው ፒኤስጂን ያስተናግዳል። የዛሬው መርሃ ግብር ሊቨርፑል የ97 ደጋፊዎቹን ሕይወት የቀጠፈውን የሂልስብሮው አደጋ 37ኛ ዓመት የሚዘክርበት በመሆኑ፣ ከጨዋታው መጀመር በፊት በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ደጋፊዎች መታሰቢያ የሚሆን ዝግጅት ይከናወናል።

ሊቨርፑል ዛሬ በአውሮፓ መድረክ ከፈረንሳይ ክለቦች ጋር ለ18ኛ ጊዜ የሚገናኝ ሲሆን፣ የ2 ለ 0 ውጤቱን ለመቀልበስ “የአንፊልድ ተዓምር” ያስፈልገዋል። ከጨዋታው በፊት በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት አሰልጣኝ አርን ስሎት በሰጡት ሐሳብ፤ “በአንፊልድ የባለፈውን ዓመት ሻምፒዮን አሸንፈን ከውድድሩ ውጪ እናደርገዋለን” ብለዋል። በምሽቱ ጨዋታ ከርትስ ጆንስ ከጉዳቱ በማገገሙ በቋሚነት ወደ ሜዳ ሊገባ እንደሚችል ይጠበቃል። በፒኤስጂ በኩል ደግሞ በጉዳት የመጀመሪያው ጨዋታ ያለፈው ብራድሊ ባርኮላ ከቡድኑ ጋር ወደ እንግሊዝ አምርቷል።

ጨዋታው በተመሳሳይ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይጀመራል፡፡