ማሻ፤ የካቲት 19/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የገቢዎች ሚኒስቴር ብልሹ አሰራር እና ሙስናን መከላከል የሚያስችል የጥቆማ እና የቅሬታ ማቅረቢያ ቴክኖሎጂ አልምቶ ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችል ግምገማ እያካሄደ ይገኛል።
በገቢው ዘርፍ እየተከሰቱ ያሉ የስነ-ምግባር እና ብልሹ አሰራሮችን በተገቢ ደረጃ መቅረፍ ፣ ማረም እና የዘርፉን መልካም ገፅታ መገንባት የሚቻለው በሀገር አቀፍ ደረጃ ግብር ከፋዩ ማስረጃን መሰረት ያደረገ ጥቆማ ሲሰጥ በመሆኑ ለዚህ ጥቆማ መስጫ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ አስተማማኝ ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል ስራ መሰራቱን የገቢዎች ሚኒስቴር የተቋማዊ ስጋት ስራ አመራር እና ስነ-ምግባር ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ደስታ ገልጸዋል።
በማያያዝም ይህ የጥቆማ መስጫ እና መቀበያ ቴክኖሎጂ ቀደም ሲል የነበሩ በድምፅ፣ በፅሁፍ እና በአካል
ይሰጡ በነበሩ የጥቆማ የመስጫ መንገዶች በተጨማሪነት በመምጣቱ የሚሰጡ ጥቆማዎችን እና ቅሬታዎችን ቁጥር የሚያሳድግ መሆኑን አክለዋል።
በተጨማሪም ቴክኖሎጂው ከፌደራል እስከ ክልል ባሉ በዘርፉ የተከሰቱ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን በተቀናጀ ሁኔታ በመከታተል እርምጃ እንዲወሰድ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር የመረጃ እና ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ቴክኖሎጂውን ያለማ ሲሆን በውይይቱ በዳይሬክቶሬቱ የሶፍት ዌር ቡድን አስተባባሪ አቶ ታሪኩ ዘርፉ እና የሶፍት ዌር አልሚ ባለሙያ አቶ ሃፍቱ ግርማይ ስለ ቴክኖለጂው አሰራርና ገፅታ ገለፃ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በመድረኩ ላይ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መ/ቤት እና ሁሉም ቅርንጫፎች የስጋት ስራ አመራር ኃላፊዎች እንዲሁም የክልል ገቢዎች ቢሮ የስጋት ስራ አመራር ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
More Stories
የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት ዳግም ያረጋገጡ አዲስ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች…
በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የበልግ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ያገኛሉ ተባለ
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ ከኢራን ጋር ድርድር ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ ሰጡ