ማሻ ፣ የሀምሌ 25፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በበይነ መረብ አማካኝነት በአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ማሰባሰብ ጀምሯል፡፡
በዚህም በበይነ መረብ በተደረገው ውይይት ከግብፅ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቦስትዋና እና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አረዓያ (ፕ/ር) ኮሚሽኑ እስካሁን ስላከናወናቸው ስራዎች እንዲሁም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የበይነ መረብ መድረኩ ዓላማ ከአፍሪካ ሀገራት ዲያስፖራ ማህበረሰብ አጀንዳ መቀበል እና በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ጉባኤ ተሳታፊዎችን የሚመርጡ ኮሚቴዎችን ማደራጀት እንደሆነ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) አብራተዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የአፍሪካ ሀገራት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የአጀንዳ ሃሳቦቻቸውን በቀጥታ ያቀረቡ ሲሆን÷ በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ጉባኤ የሚወክሏቸውን ተወካዮች ስለሚመርጡበት ሂደት ሀሳብ እና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከተሳታፊዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ኮሚሽኑ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ በበይነ መረብ፣ በኢሜል እና በተመረጡ ሀገራት በአካል በመገኘት አጀንዳዎችን እንደሚያሰባስብ ገልጿል፡፡
በቅርቡም ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ ከዳያስፖራው ጋር ተወያይቶ አጀንዳዎችን ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በተመረጡ የአውሮፓ፣ አሜሪካ እና እስያ ሀገራት በአካል በመገኘት ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ውይይት በማድረግ አጀንዳዎችን እንደሚያሰባስብም ተመላክቷል፡፡
በየሀገራቱ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት በጋራ በመደራጀት ለሀገራቸው የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን እያሰባሰቡ እንዲጠብቁም ኮሚሽኑ ጥሪ ማቅረቡን አቶ ጥበቡ አመላክተዋል፡፡
ፋና
More Stories
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የዘርፍ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2017 በጀት አመት የአስፈፃሚ አካላት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ማህበረሰቡ በከባድ ዝናብ ምክንያት ከሚከሰቱ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።
የሰው ተኮር ተግባራት በማጠናከር ሁለተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ገለፁ።