ማሻ ፣ የሰኔ 25፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም)የኢትዮጵያ መንግሥት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ ስር ከኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር የዕዳ ሽግሽግ የመግባቢያ ሰነድ ላይ ከስምምነት መድረሱን የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
ስምምነቱ እ.አ.አ ማርች 2025 በመርሕ ደረጃ የተደረሰውን የብድር ሽግሽግ በይፋ ተግባራዊ የሚያደርግ እና ለሀገሪቱ የ3.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ዕዳ የክፍያ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህም ለዓመታት ሲደረግ ለነበረው ድርድር ስኬታማ መቋጫ ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የመንግሥት ዕዳ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነም ነው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የገለጸው።
ኢትዮጵያ የኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ አባላትን፣ በተለይም የኢትዮጵያን የዕዳ ሽግሽግ ጥረት በማገዝ ላሳዩት ጽኑ ድጋፍ እና ትብብር፣ የኮሚቴው የጋራ ሰብሳቢዎች ለሆኑት ቻይና እና ፈረንሳይ ልባዊ ምስጋናዋን አቅርባለች።
የመግባቢያ ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ ስምምነቱ ከእያንዳንዱ የኮሚቴው አባላት ጋር በሚደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች አማካኝነት ተግባራዊ ይሆል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ስምምነቱን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ፣ “በእስካሁኑ ሂደት የተንፀባረቀው የትብብር መንፈስ በሁለትዮሽ ስምምነቶች ሂደት ወቅትም እንደሚቀጥል እና ሂደቱን ለማፋጠን እንደሚረዳ የጸና እምነት አለን” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከውጭ አበዳሪዎች ጋር በቅን ልቦና መሥራቷን እንደምትቀጥልም ገልጸዋል።
ከሀገሪቱ የዕዳ ሽግሽግ ፍላጎት እና ሁሉንም አበዳሪዎችን በተነጻጻሪ መንገድ ከማስተናገድ መርሕ ጋር በሚጣጣም መልኩ ስምምነቶችን ለመፈፀም እንጥራለን ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከኦፊሴላዊ አበዳሪ ኮሚቴው ጋር የተደረሰውን መግባቢያ፣ የቦንድ ባለቤቶችን ጨምሮ ከሌሎች የውጭ አበዳሪዎች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ የምታደርገውን ጥረት የበለጠ እንደሚያጠናክር ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል።
ኢቢሲ
More Stories
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከዳያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳ ማሰባሰብ ጀመረ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የዘርፍ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2017 በጀት አመት የአስፈፃሚ አካላት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ማህበረሰቡ በከባድ ዝናብ ምክንያት ከሚከሰቱ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።