May 3, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኩፍኝ በሽታ ለተለያዩ በሽታዎች ከማጋለጥ ባሻገር እስከሞት ድረስ የሚያደርስ በሽታ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ።

ማሻ ፣ የሚያዝያ 24፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የሸካ ዞን ጤና መምሪያ የኩፍኝ በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ለመስጠት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ስልጠና እየሰጠ ነዉ።

በሸካ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶችና ህጻናት ጤናና ስርዓተ ምግብ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተገኝ ገቦ ከግንቦት ስድስት እስከ አስራ አምስት ቀን 2017 ዓ.ም ለተከታታይ 10 ቀናት እድሜያቸው ከዘጠኝ ወር እስከ አምስት አመት ለሆናቸዉ ህጻናት የኩፍኝ በሽታን መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ይህንንም ክትባት በአስፈላጊው ሁነታ ለማዳረስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው የተገለጽ ሲሆን ከነዚህም አንዱ እየተሰጠ ያለዉ የአሰልጣኞች ስልጠና መሆኑ ተመላክቷል።

እ.አ.አ በ2023 በተደረገዉ ጥናት በአለማችን እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑና የኩፍኝ በሽታ ክትባት ያልወሰዱ ህጻናት 95 በመቶ በሽታ ላይ እንደሚወድቁ የሸካ ዞን ጤና መምሪያ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ገረመው ጭቶ ስልጠና በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል።

በዚህ የክትባት ጊዜ ዉስጥ በዞኑ ባሉ እድሜያቸው ከ5 አመት በታች የሆኑ 41ሺህ 47 ህጻናትን ለመከተብ መታቀዱም ተመላክቷል።

የኩፍኝ በሽታ ለተለያዩ በሽታዎች ከማጋለጥ ባሻገር እስከሞት ድረስ የሚያደርስ መሆኑን ወላጆች በመገንዘብ ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡም ጥሪ አቀርቧል።

ለሶስት ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ላይ የሁሉም መዋቅር የጤና ጽ/ቤት ሀላፊዎች፣ በዘርፉ የጤና ባለሙያዎች፣ እንድሁም የዞን ጤና ማናጅመንት አባላትና ለሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።