ማሻ ፣ የመጋቢት 24፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የመጋቢት 24 ፍሬዎች በሁሉም የኢትዮጵያ መንደሮች እንዲዳረሱ ተግተን እንሰራለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 7ኛ ዓመት (መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም) በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመጋቢት 24ን ፍሬዎች በየአንዳንዱ የኢትዮጵያ መንደሮች ለማድረስ ተግተን እንሰራለን በማለት ገልጸው፥ በሚወረወሩብን ድንጋዮች ብልጽግናን እንገነባበታለን ብለዋል።
መጋቢት 24 ትናንትና ዛሬን፣ ዛሬንና ነገን፣ የዳርና የመሐልን፣ ግንባርና አጋርን፣ አርሶና አርብቶ አደርን፣ ግለሰብና ቡድንን፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ ማንነትን፣ በመደመር ዕሳቤ ያግባባች በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ ያላት ቀን ናት ብለዋል፡፡
በመደመር ጎዳና ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማድረስ የተጀመሩት ሥራዎች ፍሬያቸውን ማሳየት መጀመራቸውን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ተገቢዋን ቦታ ለመያዝ ተቃርባለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በድህነትና ኋላቀርነት ይነሳ የነበረው ስሟ በስንዴ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የቱሪስት መዳረሻ ምቹ ቦታዎች፣ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በጎ ገፅታዎች መጠራት መጀመሩን አንስተዋል፡፡
በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር፣ በገበታ ለትውልድ አማካኝነት ሀገር የሚቀይሩ ፕሮጀክቶች ተጀምረው እንዲጠናቀቁና ከዕዳ ወደ ምንዳ ለመጓዝ መጋቢት 24 መነሻ ሆናለች ሲሉም አውስተዋል፡፡
በመጋቢት 24 ለመፍጠርና ለመፍጠን የሚያስችል ዐውድ መዘርጋቱንና እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ሐሳቦች ከዕንቅፋት ተርፈው ለብርሃን መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፥ አረንጓዴ ዐሻራ፤ የሌማት ትሩፋት፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የትምህርት ቤት ምገባንና የኮሪደር ልማትን የመሳሰሉ ተነሳሽነቶች የመጋቢት 24 ውጤቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህን የመጋቢት 24 ፍሬዎች መንከባከብና ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ፍሬዎችን ከጃርቶችና ከቀበሮዎች መጠበቅ አለብን፥ ማንም ከመዳረሻችን አያስቀረንም ብለዋል፡፡
ፋና
More Stories
ማህበረሰቡ በከባድ ዝናብ ምክንያት ከሚከሰቱ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።
የሰው ተኮር ተግባራት በማጠናከር ሁለተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ገለፁ።
የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ያሳድጋል