May 31, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የግል ጄታቸውን ለሕዝብ አምቡላንስ አገልግሎት የለገሱት ጋናዊው ቱጃር

አዲስ ዕቃ ሲገዛ የቀድሞውን መሸጥ ወይም ለሌላ የግል ጥቅም ማዋል የተለመደ ቢሆንም፣ በምዕራብ አፍሪካ ታዋቂ የቢዝነስ ሰው ኢብራሂም ማሃማ ግን ነገሩ ከዚህ የተለየ ሆኗል።

ባለሀብቱ በቅርቡ እጅግ ዘመናዊ የሆነውን ‘Bombardier Global 6500’ የግል ጄት መግዛታቸውን ተከትሎ፣ የቀድሞውን የግል አውሮፕላናቸውን ለሀገሪቱ ሕዝብ የአየር አምቡላንስ አገልግሎት እንዲውል በነፃ መለገሳቸውን ይፋ አድርገዋል።

ይህ አስደናቂ የበጎ አድራጎት ተግባር በአክራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱን ጄታቸውን በተረከቡበት ወቅት የታወጀ ሲሆን፣ አውሮፕላኑ ያለምንም ክፍያ ለማንኛውም ጋናዊ የሕክምና ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት እንዲሰጥ መበርከቱን የሀገሪቱ ብሔራዊ የዜና ማሰራጫ (GBC) በሰፊው ዘግቦታል።

ይህ ድንቅ ልገሳ የኢብራሂም ማሃማ የመጀመሪያው የቸርነት ሥራቸው አይደለም። ላለፉት 30 ዓመታት በማዕድን፣ በኮንስትራክሽን እና በግብርና ዘርፍ የተሰማሩትና በቅርቡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተሰጣቸው ባለሀብቱ፣ ከዚህ ቀደም ከ20 ሺህ በላይ ቤቶችን በመገንባት ለአቅመ ደካሞች በነፃ ማስተላለፋቸው ይነገራል።

በተጨማሪም በኩላሊት ሕመም ትሰቃይ ለነበረች የ13 ዓመት ታዳጊ የ25 ሺህ አሜሪካ ዶላር የሕክምና ድጋፍ በማድረግ ሕይወቷን በማትረፍ በጎነታቸውን በተግባር አሳይተዋል።

አሁን በነፃ የለገሱት የአየር አምቡላንስ በጋና የጤና ዘርፍ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የሚደረገውን የመንግሥት ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ ሲሆን፣ ሀብትን ለወገን ደራሽነት በማዋል ረገድ ለሌሎች ባለሀብቶች ታላቅ አርአያ የሚሆን ተግባር ሆኖ ተመዝግቧል።