የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የአፍሪካ ኩራት” መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ፣ አህጉሪቱን እርስ በእርስና ከቀሪው ዓለም ጋር በማገናኘት ረገድ ግንባር ቀደም ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት በ40 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ወደሚገኙ ከ60 በላይ ከተሞች የበረራ አገልግሎት በመስጠት፣ የአህጉሪቱን የኢኮኖሚና የቱሪዝም ትስስር ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
ከ60 በላይ የአፍሪካ እንዲሁም ከ145 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት አየር መንገዱ፣ አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት በማገናኘት ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ይዟል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በቅርቡ በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ተቋሙ ራሱ ትርፋማ ከመሆን ባለፈ ሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶችም አብረውት እንዲያድጉ በትብብር እየሠራ ይገኛል።
በተለይም በቶጎው አስካይ (ASKY)፣ በማላዊ፣ በዛምቢያ እና በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አየር መንገዶች ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ በመያዝ እና የማኔጅመንት አገልግሎት በመስጠት ስትራቴጂካዊ አጋርነቱን አጠናክሯል።
ይህም አህጉራዊ ትስስርን ለማጠናከር ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም ሆኗል።
ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ አዳዲስና ትናንሽ አየር መንገዶች ከአውሮፕላን አከራዮች ጋር ያላቸውን የመደራደር አቅም ለማገዝ አውሮፕላኖችን ተከራይቶ በድጋሚ በማከራየት ትልቅ ድጋፍ እያደረገ ነው።
አከራዮች ለአዳዲስ አየር መንገዶች ያላቸውን የመተማመን ክፍተት ለመሙላት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋስትና ሆኖ ማገልገሉ ለአህጉሪቱ አቪዬሽን እድገት መፋጠን የጎላ አስተዋፅዖ አለው።
ይህ አጋርነት አየር መንገዱ ለአህጉሪቱ ዕድገት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ተግባር ተደርጎ ተወስዷል።
የአየር መንገዱ እህት ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ለአየር መንገዱ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ አብራሪዎችን፣ የቴክኒክ ባለሙያዎችን እና የአየር መንገድ አስተናጋጆችን በማሰልጠን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎትን እየሸፈነ ይገኛል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው ግዙፍ የጥገና ማዕከል (MRO) ደግሞ የአፍሪካ አውሮፕላኖች ለጥገና ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉዞ በማስቀረት፣ ጥራት ያለው አገልግሎት እዚሁ አህጉራችን ላይ እንዲያገኙ በማድረግ የውጭ ምንዛሬን እያዳነ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ በማድረግ አየር መንገዱ ከካርቦን ልቀት የጸዳ የሳፍ (SAF) ነዳጅ አጠቃቀምን ለማስፋፋት ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ሽርክና በመፍጠር ላይ ይገኛል።
ይህም አየር መንገዱ ለአካባቢ ጥበቃና ለዘላቂ እድገት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳያል።
የአፍሪካ ሕብረት በአህጉሪቱ ነፃ የአየር ትራንስፖርት እውን ለማድረግ ለያዘው ፕሮጀክት የላቀ አስተዋጽኦ በማድረግና በሌሎች ስኬቶቹ አየር መንገዱ በተደጋጋሚ ተሸላሚ መሆኑ ይታወሳል።
More Stories
የሸካ ህዝቦች ልማት ማህበር የጀመረው የሰንበት ገቢያ በበዓል ወቅት ከሚፈጠረው የዋጋ ንረት ታድጎናል ሲሉ የሸካ ዞን ማሻ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ሩሲያ ከመጋቢት 23 ጀምሮ የነዳጅ (ቤንዚን) ኤክስፖርት ልታግድ ነው።
የቡና ምርትን ለዓለም ገበያ በማቅረብ 43 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡- የኦሮሚያ ቡና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒየን