April 20, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የአሜሪካ ተወካዮች ለተጨማሪ ድርድር ወደ ኢስላማባድ እያመሩ መሆኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ

አሜሪካና እስራኤል ከኢራን ጋር የገቡበትን የጦርነት ቀውስ ለመፍታት፣ የአሜሪካ ተወካዮች ለተጨማሪ ድርድር ወደ ፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ እያመሩ መሆኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ የአሜሪካ ተወካዮች ለድርድር ነገ ምሽት ኢስላማባድ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የልዑካን ቡድናቸው ወደ ኢስላማባድ እንደሚጓዝ ቢያረጋግጡም፣ ኢራን በበኩሏ በዚሁ ድርድር ላይ ስለመገኘቷ እስካሁን በይፋ ያረጋገጠችው ነገር የለም።

ይህ የሁለተኛ ዙር የኢስላማባድ ንግግር፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጥልቅ ልዩነት ለመፍታትና ቀጣይነት ያለው የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለመ መሆኑ ተመልክቷል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ለኢራን “በጣም ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ” የሆነ የሰላም ስምምነት ማቅረቧን ገልጸው፣ የኢራን ወገን ስምምነቱን እንደሚቀበለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንቱ ድርድሩ ስኬታማ ካልሆነ ግን አሜሪካ ወደማይቀለበስና ጠንከር ያለ የኃይል እርምጃ እንደምትገባ አስታውቀዋል።

ኢራን ስምምነቱን የማትቀበል ከሆነ፣ አሜሪካ በኢራን የሚገኙ እያንዳንዱን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና ድልድዮች ላይ ድብደባ እንደምትፈፅም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

BBC