April 20, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

“የትግራይ ወጣት የፖለቲካ ሴራዎችን ተረድቷል፤ ከአሁን በኋላ የጦርነት መሣሪያ አይሆንም”፦ የቀድሞዋ አፈ-ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም

በትግራይ ወጣቶች ዘንድ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የአመለካከትና የንቃት ለውጥ እየታየ መሆኑን የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ገለጹ።

ወጣቱ አሁን ላይ የፖለቲካ ሴራዎችን በመረዳት “ለጥቂት ግለሰቦች ስልጣን ሲባል አልሞትም” የሚል ጠንካራ አቋም እየያዘ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

ወይዘሮ ኬሪያ ከኢቢሲ የ”ስለ ሀገር” ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳመለከቱት፣ በትግራይ የሚገኘው ወጣት ካለፈው የጦርነት መከራ በመማር አሁን ያለውን የጦርነት ነጋሪት በንቃት እየተቃወመ ይገኛል።

ወጣቱ ቀደም ሲል “ለህዝብ ህልውና” ተብሎ ይነገረው የነበረው ትርክት፣ አሁን ላይ “የጥቂት መሪዎችን ስልጣን ለማስጠበቅ” የሚደረግ ድራማ መሆኑን በውል ተረድቷል ብለዋል። “ወጣቱ የነሱን ህልውና ለማረጋገጥ መሞት እንደሌለበት ገብቶታል” ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፣ ይህ ግንዛቤ በሕወሃት ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩን ገልጸዋል።

የትግራይ ወጣቶች ማህበራዊ ትስስር ገጾች በግልጽ ቋንቋ እየዘፈኑ  “ጦርነት ይበቃናል፤ ሰላም እንፈልጋለን” እያሉ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይም ወጣቶች ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውንና የሰላም ናፍቆታቸውን መግለጻቸው፣ ከአሁን ቀደም ከነበረው በብሔር የመሸሸግ ዝንባሌ ላላቸው የማይመች መሆኑን አስረድተዋል።

በትግራይ እናቶችና ወጣቶች ዘንድ ትልቅ ሐዘንና ቁጭት መኖሩን የገለጹት ወይዘሮ ኬሪያ፣ አንዲት ወጣት በትግርኛ የተናገረችውን ድምፅ ዋቢ በማድረግ “ለእናቴ ጀግና ሆኜ መሞት ሳይሆን፣ ጀግና ሆኜ መኖርና እናቴን መርዳት እፈልጋለሁ” የሚለው ድምፅ የብዙኃኑ ወጣት ጽኑ አቋም መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ግን ወጣቱ ሐቅን መቀበል መጀመሩንና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ መሪዎቹን መሞገት መጀመሩ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የወጣቱ የአመለካከት ለውጥ በትግራይ ያለውን የኃይል ሚዛን እንደሚያስተካክለውና ለዘላቂ ሰላም መምጣት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

EBC