March 16, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አዲስ የብልጽግና መንገድ እያሳየች ነው:- ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ


ማሻ፤ መጋቢት 8/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) ታዋቂው የኢኮኖሚክስ ምሁርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካሪ ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ፣ ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለመላው አፍሪካ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገለጹ።

ምሁሩ ከኢቲቪ አዲስ ዳያሎግ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ተቋማት የ3 እና 4 በመቶ የዕድገት ትንበያ ታስረው መቅረት እንደሌለባቸው ጠቁመው።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በሌሎች የቁጠባ ፖሊሲ ሳትገደብ ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት እንደሚቻል በተግባር እያሳየች መሆኑን በአድናቆት ተናግረዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ የስኬት ምስጢር ግልጽ በሆነ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መመራቷ ነው።

በተለይም በመሠረተ ልማት፣ በኃይል አቅርቦትና በዲጂታል ሽግግር የታዩ ለውጦች ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገሯት ይገኛሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ የመገንባት ዕቅድ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል እንደሚያደርጋት ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል።

ይህ ግስጋሴ ኢትዮጵያ በቀጣናው ለሚደረገው የኢኮኖሚ ትስስር ጠንካራ ምሰሶና ተምሳሌት ሆና እንድታገለግል የሚያስችላት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ ለአፍሪካ ሀገራትም በትጋት ሰርቶ ማደግ እንደሚቻል ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።