March 13, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ሚኒስቴሩ ለሦስት ኩባንያዎች የማዕድን ምርት ፍቃድ ሰጠ

ማሻ፤ መጋቢት 4/2018 ዓ/ም(ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) ማዕድን ሚኒስቴር በተለያዩ የማዕድን ምርት ለሚሰማሩ ሦስት ኩባንያዎች የምርት ፍቃድ ሰጥቷል፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያላትን ሀብት በተገቢው መንገድ ለማልማት ወሳኝ ርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች፡፡

ለኩባንያዎቹ ፍቃድ መሰጠቱ ማዕድናቱን ወጥነት ባለው መልኩ ለማምረትና ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ስትራቴጂያዊ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የምርት ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ፍቃድ የተሰጣቸው ኩባንያዎች በፖታሽ፣ በብረትና በወርቅ ማዕድን ምርቶች የሚሰማሩ ሲሆን፥ ሦስቱም የማዕድን ምርቶች 2 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ወጪ የሚደረግባቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት በፖታሽ ምርት ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ፣ በብረት ምርት ለዜድዋይቲ ቢዲአይኤም (ZYTBDIM) እንዲሁም በወርቅ ምርት ለቤሮ ማይኒንግ የማዕድን ምርት ፍቃድ ተሰጥቷል፡፡

(ኤፍ ኤም ሲ)