የዓለም የቡና ዋጋ በመቀነሱ አቅራቢዎች በእጃቸው ያለውን ምርት በፍጥነት ለገበያ እንዲያቀርቡ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አሳሰበ።
ባለስልጣኑ ዓለም አቀፉን የቡና ገበያ ሁኔታና የኢትዮጵያን ቡና ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
ይህንን የዋጋ መዋዠቅ ተከትሎ፣ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለቡና አቅራቢዎች፣ ላኪዎችና አርሶ አደሮች ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላልፈዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ሀገሪቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ቡና ያመረተች መሆኑን ያነሱት ዶክተር አዱኛ፤ ከዚህ ውስጥ 600 ሽህ ቶን የሚሆነውን ወደ ውጭ በመላክ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳ እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።
እንደ ዶክተር አዱኛ ገለፃ ፤ ባለፉት ሁለት ወራት የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ከነበረበት 4 ዶላር ወደ 2 ነጥብ 8 ዶላር ዝቅ ብሏል፡፡
በቀጣይም እስከ 2 ነጥብ 5 ዶላር ሊወርድ እንደሚችል መተንበዩ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳርፏል ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በነበረው ከፍተኛ ዋጋ ምክንያት አቅራቢዎች ቡና ገዝተው ያከማቹ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የዓለም የቡና ገበያ እየቀነሰ በመምጣቱ ምርቱን በእጃቸው ያቆዩ አካላት ለከፍተኛ ኪሳራ እንዳይደረጉ ያላቸውን ቡና አሁን ባለው የገበያ ዋጋ በፍጥነት ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡና ወደ ውጭ እንዲልኩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቡናን ከአንድ ዓመት በላይ አሳድሮ ማቆየት፣ በኮንትሮባንድ ወይም በህገ-ወጥ መንገድ ለመሸጥ መሞከር በህግ የሚያስቀጣ መሆኑን አንስተው፤ ሀገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ የሚያሳጣ ተግባር መሆኑንም አመልክቷል።
አቅራቢዎች የዘመኑን መረጃና ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዓለም ገበያውን በንቃት እንዲከታተሉና ከኮሜርሻል ቡና ይልቅ የተሻለ ዋጋ በሚያስገኘው የስፔሻሊቲ ቡና ጥራት ላይ እንዲያተኩሩም አሳስበዋል።
More Stories
የሸካ ህዝቦች ልማት ማህበር የጀመረው የሰንበት ገቢያ በበዓል ወቅት ከሚፈጠረው የዋጋ ንረት ታድጎናል ሲሉ የሸካ ዞን ማሻ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ሩሲያ ከመጋቢት 23 ጀምሮ የነዳጅ (ቤንዚን) ኤክስፖርት ልታግድ ነው።
የቡና ምርትን ለዓለም ገበያ በማቅረብ 43 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡- የኦሮሚያ ቡና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒየን