ኢራን ዛሬም የተጠናከረ ጥቃቷን በእስራኤል፤ በአሜሪካን የጦር ሰፈሮች እና በአካባቢዋ በሚገኙ ሃገራት ላይ ቀጥላለች። ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን የጦር መርከብ ላይ ላደረሰችው ጉዳትም መራር ሀዘን ይገጥማታል ስትልም ዝታለች። በጥቃቱ መርከቧ በህንድ ውቅያኖስ የመስጠም አደጋ እንደገጠማት በዚህም 87 የኢራን ባሕረኞች መሞታቸው ተገልጿል። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ የአሜሪካ የባሕር ኃይል የኢራንን መርከብ በማስጠም የባሕር ላይ ጭፍጨፋ ፈጽሟል ሲሉ ከሰዋል። ለዚህ ደርጊቱም ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ዋጋ ትከፍላለች ሲሉም በማኅበራዊ መገናኛ ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ የኢራን ጦር አዘርባጃን ላይ ጥቃት አላደረስኩም ብሏል። አዘርባጃን ግን ሁለት የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት አድርሰው ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውን ዛሬ አስታውቋል።
ኢራን ጥቃት ማድረሷን ብትቀጥልም አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ ዋና ከተማ ቴህራንን ጨምሮ በተለያዩ የኢራን ግዛቶች ላይ የተጠናከረ ጥቃት እያደረሱ መሆኑ እየተዘገበ ነው። በተለይም የሚሳኤል ማምረቻ እና የኒኩሊየር ተቋማቷ ዋነና ኢላማዎች ተደርገዋል።
የእስራኤል ጦር ኃይል በበኩሉ ባለፉት 24 ሰዓት ሊባኖስ ውስጥ ከኢራን ጋር ትስስር ባለው የሂዝቦላኽ 80 ይዞታዎች ላይ ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል። ኢራን ላይም በቀጠለው ጥቃት የረዥም ርቀት ቦለስቲክ ሚሳኤል መተኮሻ ስፍራዎችንና ሌሎች ኢላማዎችን መደብደቡን አመልክቷል።
ዋሽንግተን እና ቴል አቪቭ ባለፈው ቅዳሜ ድንገት በኢራን ላይ በከፈቱት ጥቃት የሀገሪቱ ሃይማኖታዊ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ መገደላቸውን ተከትሎ በተባባሰው ጦርነት ከ1,200 በላይ ሰዎች ኢራን፤ ከ70 የሚበልጡ በሊባኖስ እንዲሁም በርካቶች እስራኤል ውስጥ መገደላቸውን የአሶሲየትድ ፕረስ ዘገባ ያስረዳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በተባባሰው ጦርነት ምክንያት በረራዎች ከተስተጓጎለበት የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ሃገራት ዜጎቻቸውን ለማስወጣት እየሞከሩ ነው። ጀርመን በዛሬው ዕለት የመጀመሪያ በተባለው በረራ በርካታ ዜጎቿን ወደ ሀገር አስገብታለች። ከኦማን የተነሳው የጀርመን ሉፍትሃንዛ አውሮፕላን ፍራንክፈርት ደርሷል።
More Stories
ታሪካዊ ስህተትን የማረም ጉዞ …
በሸካ ዞን የማሻ ወረዳ ም/ቤት በ4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት የስራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባኤው የ2018 የ6 ወራት አፈጻጸም መድረክ አካሂዷል።
ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር በዜጎች ማህበራዊ ሕይወት ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር በማድረግ ክልላዊና ሀገራዊ ግቦችን ማሳካት እንደሚገባ ተገለፀ ።