March 3, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የብልፅግና ፓርቲና መንግስት  በሰው ተኮር ፕሮግራሞች ዜጎች ምቹ በሆኑ አከባቢዎችና  የመኖሪያ መንደሮች እንዲኖሩ አበክሮ ይሰራል_ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ

ማሻ፤ የካቲት 24/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የኢፌዴሪ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ያስገነባውን ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት አስመርቆ ቁልፍ አስረክቧል።

በመርሃ ግብሩ የተገኙ የኢፌዴሪ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ የብልፅግና ፓርቲና መንግስት  በሰው ተኮር ፕሮግራሞች ዜጎች ምቹ በሆኑ አከባቢዎችና  የመኖሪያ መንደሮች እንዲኖሩ አበክሮ ይሰራል ብለዋል።

የማህበራዊ ልማት ስራዎችን ለማረጋገጥ መንግስት እያደረገ ከሚገኘው ብርቱ ጥረት ባሻገር የማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል።

የተለያዩ ግለሰቦችንና የባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እንደዚህ አይነት የበጎነት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ በክልሉ በ2017 በክረምት በጎ ፊቃድ የተሰሩ የአቅመ ደካማ ቤቶች ትልቅ እውቅናና ምስጋና የሚገባ መሆኑን አስረድተዋል።

በታርጫ ከተማ አስተዳደር በበጎ ፊቃድ አገለግሎት ግንባር ቀደም የሆኑና ለሌሎች አከባቢዎች ተሞክሮ የሚሆኑ ተግባራት ተከናውኗል ያሉት ወ/ሮ ገነት ለከተማ አስተዳደሩ ምስጋና አቅርበዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው እንደዚህ አይነት በጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ የተጀመሩ ኢንሼቲቮችን ወደ ዞኑ ሁሉም አከባቢዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው የሚኒስቴር መስሪያ ቤትን አመስግነዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገነቡ ቤቶች 3 አባዎራዎችንና 2 እማወራዎችን በአጠቃላይ 20 የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ 24 ሰዓት ኤሌክትሪክ ማስጠቀም የሚያስችል ሶላር ሲስተም የተገጠመለት፣ ሽንት ቤትና ሌሎች መሠረታዊ ቁሳቁሶች የተሟላ እንደሆነ ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ የክልሉ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ፣ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ፣ የታርጫ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አስናቀ አበበ እንዲሁም ሌሎች የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

#SWMN