February 15, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ቤኒሻንጉል እና ጋምቤላ ክልል በምዘና ውድድሩ ትክክለኛ ዕድሜ በማሳተፍ በተሻለ አፈፃፀም አሸናፊ ሆኑ።

ማሻ፤ የካቲት 8/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ቤንሻንጉል እና ጋምቤላ ክልል በትክክለኛ የዕድሜ ተሳትፎ ከ1-3 በመሆን በአሸናፊነት አጠናቀቁ።

ከ13 እስከ 15 ዓመት በታች የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር ለሳምንት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ያገናኘው የወንዶች እግር ኳስ የፍፃሜ ጨዋታ 1ለ0 በማዕከላዊ ኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በምዘና ውድድሩ በኦሎምፒክ ስፖርቶች አማራ ክልል በ38 ወርቅ፣ 33 ነሀስ እና 22 ብር 1ኛ ሆኖ አጠናቋል።

ኦሮሚያ ክልል በ31 ወርቅ፣ 30 ብር እና በ21 ነሀስ 2ኛ ሲሆን አዲስ አበባ በ30 ወርቅ፣ 33 ብር፣ 33 ነሀስ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በፓራሊምፒክ ስፖርት ኦሮሚያ ክልል በ34 ወርቅ፣ 34 ብር፣ 26 ነሀስ 1ኛ በመሆን አሸናፊ ሆኗል።

አዲስ አበባ በ21 ወርቅ፣ 23 ብር እና 16 ነሀስ 2ኛ ሲሆን አማራ በ12 ወርቅ ፣በ6 ብር እና በ 3 ነሀስ 3ኛ ደረጃን ይዞ ይዟል።

መስማት በተሳናቸው አዲስ አበባ 10 ወርቅ፤ 5 ብር፣ 5 ነሃስ 1ኛ፣ ኦሮሚያ በ6 ወርቅ፣ 8 ብር ፣ 8 ነሃስ 2ኛ ሲሆን አማራ በ5 ወርቅ፤ 3 ብር 6 ነሃስ 3ኛ ደረጃን ይዟል።

ለኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እና ለተለያዩ ስፖርት አካዳሚዎች ታዳጊ ስፖርተኞችን ያስመለመሉ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሸላሚ ሆነዋል።

በዚሁ መሠረት ደቡብ ኢትዮጵ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 26 ስፖርተኞችን በማስመልመል 1ኛ ሲሆኑ
ጋምቤላ ክልል 24 ታዳጊዎችን በማስመረጥ 3ኛ ሆኗል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርታዊ ጨዋነትን ዋንጫ ወስዷል።

በምዘና ውድድሩ 80 ወንድና 86 ሴት ታዳጊ ስፖርተኞች በአጠቃላይ 165 ስፖርተኞች ተመልምለዋል