December 17, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ሕፃናት ወደ አፋቸው የሚያስገቧቸው ባዕድ ነገሮች እስከ ሞት ለሚያደርስ አደጋ እያጋለጣቸው ነው፦ የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት

ማሻ ፣ የሰኔ 12፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) ሕፃናት ያገኙትን ነገር ወደ አፋቸው የማስገባት ልማድ አላቸው፤ ያም ብቻ ሳይሆን ወደ አፋቸው ያስገቡትን ነገር ድንገት የሚውጡባቸው ጊዜያት አሉ።

ታዲያ ሕፃናቱ በቂ ክትትል ካልተደረገላቸው ወደ አፋቸው አስገብተው በዋጡት ባዕድ ነገር ምክንያት ከአካል ጉዳት እስከ ሕይወት ማለፍ አደጋ ሲደርስባቸው ይስተዋላል።

በተለይ ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 5 ዓመት ያሉ ሕፃናት በቤት ውስጥ በሚጫወቱበት ጊዜ የሚያገኟቸውን መጫወጫዎች፣ ትናንሽ የሰዓት ባትሪዎች፣ ሳንቲሞች እንዲሁም ሌሎች ባዕድ ነገሮችን ወደ አፋቸው የሚከትቱ በመሆኑ ከፍተኛ ትክክትል ይፈልጋሉ።

ኢቢሲ ዶት ስትሪም የሕፃናት ባዕድ ነገሮችን ወደ አፋቸው ማስገባት አስከፊነት በሚመለከት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ከሆኑት ዶ/ር ዓባይ ጎሣዬ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ሕፃናት ጠቃሚ እና ጎጂ ነገርን ባለማወቃቸው ምክንያት ባዕድ ነገር ወደ አየር ቱቦ እንዲሁም ወደ ምግብ ቱቦ ሊያስገቡ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዳለ ነው የተናገሩት።

ይህ ደግሞ ልጆች ላይ ድንገተኛ አደጋዎችን ከሚያስከትሉ ክስተቶች መካከል ዋነኛው እንደሆነም አንሥተዋል።

ከ9 ወር ጀምሮ ያሉ ሕፃናት እንቅስቃሴ የሚጀምሩበት ወቅት በመሆኑ የሚያነሡትን ነገር ሁሉ ወደ አፋቸው ይከትታሉ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ባዕድ ነገሩ ወደ ምግብ ቱቦ ገብቶ ጉዳት ያስከትላል።

ወደ ምግብ ቱቦ በብዛት ከሚገቡት ደግሞ እንደ የሰዓት ባትሪ እና ሳንቲም ያሉ ነገሮች እንደሆኑ ነው ሐኪሙ የገለጹት።

ሳንቲሞቹ ተለቅ ያሉ በመሆናቸው አልፎ አልፎ ጉሮሮ አካባቢ ተቀርቅረው እንደሚቀሩም እና ሕፃናቱ ላይ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ነው ያብራሩት።

በጣም አንገብጋቢው እና ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለው ግን ትናንሽ ባትሪዎችን መዋጥ ነው ያሉት ዶክተር ዓባይ፣ በተለይ የሰዓት፣ የአሸንጉሊት እና የአንዳንድ ሪሞት ባትሪዎችን መዋጥ ለከፋ ችግር እንደሚያጋልጥ አብራርተዋል።

ባትሪዎቹ በባህሪያቸው የተለያየ ኬሚካል ስላላቸው ለከፋ ችግር እንደሚያጋልጧቸው ነው የጠቆሙት።

ወደ ሕፃናት ሆድ የሚገቡ ባትሪዎች በሚያርፉበት ቦታ ላይ አንጀትን እና የምግብ ቱቦን በማቃጠል እና በማበላሸት ፊስቱላም ጭምር ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ስለታማ ነገሮችን መዋጥ ለከፋ ችግር እንደሚዳርግም አስገንዝበዋል። ስለታማ ነገሮች የአየር ቱቦን በመቆራረጥ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትሉም አንሥተዋል።

እንደ ሽንብራ፣ በቆሎ፣ ለውዝ ያሉ ምግቦች ሕፃናት በመዝገን አፋቸው ውስጥ በማስቀመት ሲጫወቱ እና ሲስቁ የአየር ቱቦ ላይ በመግባት እስከ ሞት የሚደርስ የከፋ ችግርን እንደሚያስከትል ነው ያነሡት።

የኳስ መንፊያ እና የእስክሪፒቶ ክዳን እና ሌሎች ባዕድ ነገሮችን በመዋጣቸው ለሳንባ ኢንፌክሽን እና ለሌሎች በሽታዎች ሊዳረጉ ይችላሉ።

በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን ሊከታተሉ እና ሊጠብቁ እንደሚገባ መክረው ሕፃናት ማንኛው ባዕድ ነገር ከዋጡ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋማት ሊወስዶቸው እንደሚገባ ነው የመከሩት።

ኢቢሲ