August 7, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ትራምፕ የቡድን 7 ጉባዔ ሳይጠናቀቅ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

ማሻ ፣ የሰኔ 10፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ውጥረት ለመከታተል ሲሉ፤ የቡድን 7 (G7) ጉባዔ ሳይጠናቀቅ ወደሀገራቸው መመለሳቸው ታውቋል።

በካናዳ እየተካሄደ በሚገኘው የቡድን 7 ጉባዔ አጭር ቆይታ ያደረጉት ትራምፕ “በተቻለኝ ፍጥነት መመለስ አለብኝ” ሲሉ ለጋዜጠኞች መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

“በግልጽ በሚታወቁ ምክንያቶች ቀድሜ መመለስ አለብኝ” ሲሉ የተደመጡት ትራምፕ፤ በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ውጥረት ለመከታተል እና ከኢራን ጋር የሚካሄደውን ድርድር ዳግም ለማስጀመር ፍላጎት እንዳላቸው ሲኤንኤን ዘግቧል።

ትራምፕ ካናናስኪስ በተሰኘችው የካናዳ የመዝናኛ ከተማ ከመሪዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ “ኢራን በመሠረቱ ስምምነት ለማድረግ ወደ ድርድር ጠረጴዛ የቀረበች ይመስለኛል፤ እኔም ከዚህ እንደወጣሁ አንድ ነገር እናደርጋለን” ብለዋል።

ትራምፕ በተገኙባቸው ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ጉባዔው መጠነኛ መከፋፈልን ማስተናገዱ እንደተስተዋለም ከስፍራው የወጡ ዘገባዎች አመላክተዋል።

ፕሬዚዳንቱ መጀመሪያ ላይ፣ በእስራኤልና በኢራን መካከል ውጥረት እንዲረግብ የሚጠይቀውንና በቡድን 7 ሀገራት መሪዎች የተዘጋጀውን የጋራ መግለጫ ላለመፈረም ፍላጎት አሳይተው ነበር። ይሁን እንጂ፣ ትናንትና አመሻሽ ላይ ቡድን 7 ለቀውሱ መፍትሄ እንዲገኝ የሚጠይቅና የትራምፕን ይሁንታ ያገኘ የሚመስል የመሪዎች መግለጫ አውጥቷል።

ትራምፕ በተመሳሳይ እ.አ.አ. በ2018 የቡድን 7 ጉባዔን ጥለው መውጣታቸው ይታወሳል።

ኢቢሲ