June 7, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ከተፎካካር የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሀገር አንድነት እና ልማት ላይ የተጀመሩ ሁሉዓቀፍ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፦ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

ማሻ ፣ የግንቦት 29፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ”ለተረጋጋ ፖለቲካዊ ሥርዓትና ባህል ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ወሳኝ ነው” በሚል መሪ ቃል በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ሀገራዊ እና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ክልላዊ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ ለዘላቂ ሠላም የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ የሚያረጋግጡ ትላልቅ የሀገራዊ እና ክልላዊ የልማት ፕሮጀክቶች ከዳር እንዲደርሱ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

መጪው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከመንግሥት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ያነሱሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ቋንቋ እና እሴት እንዲጎለብት መሠራት ያስፈልጋል ነዉ ያሉት።

አካል ጉዳተኞችንና ሴቶችን በሁሉም ዘርፎች አካታች ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች እንዲጠናከሩም ተጠይቋል።

የህዝብን አንድነት ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሀሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ በመዉሰድ ህግ የማስከበር ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባልም ተብሏል።

ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን መከላከል፣ የስራ ዕድሎችን ማስፋት የኑሮ ውድነትና ሌሎች ማህበራዊ፣ኢኮኖሚና ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በክልሉ በህጋዊነት ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ከተፎካካር የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመደማመጥ፣በመቻቻል እና በመከባበር መንፈስ በሀገር አንድነት እና ልማት ላይ የተጀመሩ ሁሉዓቀፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል።

ምክክሩ ቤተሰባዊነትን ለማጎልበት የቻልንበት ነዉ ያሉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ለአንድ ሀገርና ህዝብ በጋራ የምናበረክተው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሀገሪቱን ሰላም ለማድፍረስ እና የህዝብን አንድነት ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ልንታገሳቸዉ እንደማይገባ ያስገነዘቡት

አቶ ሰለሞን በክልሉ የሚገኙ የዳበሩ ባህላዊ እሴቶችን በተገቢው በመጠቀም የመነጋገር እና የመደማመጥ ብሎም በጋራ የመስራት ሂደታችንን ይበልጥ ሊናዳብር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸዉ በክልሉ ተኪ እና ኤክስፖርት ምርቶችን በማምረት የተመዘገቡ ውጤቶችን ቀጣይ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።

የክልሉ እምቅ ሀብቶች በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ላይ አይነተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ያሉት አቶ ማስረሻ ይህንን ተግባር ዘላቂ ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የህብረብሔራዊ አንድነትን የሚፈታተኑ የጽንፈኝነት አስተሳሰቦችን መግራት እና ማረም እንደሚገባም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አበራ ገልጸዋል።

ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ከባባዊ ጉዳዮች ለማጎልበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡ አሳስበው ብልጽግና ፓርቲ ህዝብን በማድመጥ እያከናወነ የሚገኘውን ሁሉዓቀፍ ሥራዎች ይበልጥ እየተስፋፉ ይቀጥላሉም ብለዋል።

ክልል ኮሚኒኬሽን