May 23, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የልዑክ ቡድናቸው በፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኤሊሴ ቤተመንግሥት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ማሻ ፣ የግንቦት 15፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም)በሁለትዮሽ ውይይቱ ወቅትም ፕሬዝዳንት ማክሮን በታኅሳስ 2017 ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የተደረሱ ስምምነቶችን አፈፃፀም አብረው ገምግመዋል።

ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ዘመናት እንደ መከላከያ እና ፀጥታ፣ የባሕል ጥበቃ እና ትምህርት ባሉ ዘርፎች ጠንካራ ትስስር እና ትብብር የፈጠሩ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በፓሪስ የነበራቸው ውይይት በኢኮኖሚው መስክ የበለጠ ትብብር ለማድረግ እድሎችን የፈተሸ ነበር። ፈረንሳይ የኢትዮጵያ እዳ ክለሳ ሂደት ቁልፍ ደጋፊ እንደሆነች ይታወቃል።

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው መጠናከር ላይ አበክረው የሰሩ ሲሆን ይኽም በከፍተኛ የመሪዎች ጉብኝቶች፣ ስትራቴጂያዊ ስምምነቶች ብሎም በብዙ ዘርፎች በተጀመሩ የጋራ የሥራ ሂደቶች የታየ ሆኖ ቆይቷል።

ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ሁለቱም መሪዎች በየሀገራቱ ጉብኝቶችን አካሂደዋል። በጥቅምት 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ፈረንሳይ ተጉዘው ለተጠናከረው የመከላከያ እና የባሕል ትብብር ስምምነት መሠረት የጣለ ውይይት አድርገው ነበር።

በመጋቢት 2011 ዓ.ም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝታቸውን በማድረግ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በርካታ የትብብር ስምምነቶችን ፈርመዋል። ከስምምነቶቹም የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት እና የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት መንገድ የከፈቱ ስምምነቶች ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ፕሬዝዳንት ማክሮን ከጥገና ሥራው መጀመር አስቀድሞ ላሊበላን ጎብኝተው ነበር።

በየካቲት 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፈረንሳይን በድጋሚ የጎበኙ ሲሆን የንግድ እና ኢንቬስትመንት ትስስሮች ላይ በማተኮር ውይይቶች ተካሂደዋል። በወቅቱም ኢትዮጵያ ያላትን የተረጋገጠ ዘላቂ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ብሎም የቀጠና ሰላም አስፈላጊነት ላይ ውይይት ተካሂዶም ነበር።

በታኅሳስ ወር 2017 ዓ.ም ፕሬዝዳንት ማክሮን ወደ ኢትዮጵያ በድጋሚ መጥተው ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የእዳ ክለሳ በተመለከተ ያላትን ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠው ነበር።

በጉብኝቱ ፕሬዝዳንት ማክሮን የኢትዮጵያን የእዳ ክለሳ ሥራ በምሉእ መልክ ደግፈው የኢኮኖሚ መረጋጋት እና እድገት ለማምጣት ፈጣን መፍትሔ የመስጠትን አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተው ነበር።

ባለፉት ሰባት አመታት በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ ያለው ግንኙነት ብዝሃ ዘርፍ ወዳለው ጠንካራ ግንኙነት ተሸጋግሯል። ይኽም በሁለቱ መሪዎች የነቃ ተሳትፎ የተጠናከረ ነው።

ፋና