ማሻ ፣ የግንቦት 14፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) ኢትዮጵያ አካታች የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ስራ ማከናወኗን የአይዲ ፎር አፍሪካ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።
ለአራት ቀናት የሚቆየው አይዲ ፎር አፍሪካ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ግንቦት 12 በአዲስ አበባ መከፈቱ ይታወሳል።
ጉባዔው በዲጂታል ማንነት ግንባታ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች የሚቀርቡበት ሲሆን÷ በዲጂታል ፓስፖርትና መታወቂያ ላይም የተሻለ መፍትሄ ይዘው የመጡ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለእይታ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግና የጃፓኑ ቶፓን የጋራ ኩባንያ የሆነው ቶፓን ሴኪዩሪቲ የኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ቃልኪዳን አረጋ÷ ኩባንያው ስትራቴጂክ የሆነውን ሚስጥራዊ ህትመት ተደራሽ ለማድረግ በኢትዮጵያ ግዙፍ የህትመት ፋብሪካ እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ በዓመት ከ5 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ፓስፖርት እንደሚያመርት ጠቅሰው÷ በዚህም ምርቱን ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች ሀገራት ለማቅረብ ያስችለዋል ብለዋል።
የፓስፖርት ህትመቱ በኢትዮጵያ መከናወኑ የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት ባለፈ ደህንነቱ የተጠበቀና አገራዊ እሴትን የተላበሰ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ የሚሆን ፓስፖርት ለማቅረብ እንደሚያስችል አስታውቀዋል።
የቻይና ኢፕቴክ ኩባንያ የሽያጭ ባለሙያ ሃርበርት ጎንዶ ኩባንያው አስተማማኝ የማንነትና ደህንነት ማረጋገጫ መፍትሄዎችን እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እያሳየችው ያለው ለውጥ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው÷ ኩባንያቸውም ይህን ዕድል በመጠቀም በመላ ሀገሪቷ አገልግሎቱን ለማስፋት ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።
በሚስጥራዊ የፓስፖርትና ዲጂታል መታወቂያ ህትመት ላይ የሚሰራው የጀርመኑ ቬሪዶስ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዛቪየር ሮስት በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ዲጂታል ማንነትን ለማረጋገጥ በምትሰራው ስራ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት ብለዋል።
ኩባንያቸው ይህን ዕድል በመጠቀም በኢትዮጵያ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ ባደረገችው ዲጂታል መታወቂያ ውጤታማ ሆናለች ያሉት ደግሞ በሚስጥራዊ ዶክመንቶች ህትመት ላይ የተሰማራው ኢን ግሩፕ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አኜ ዲአሎ ናቸው።
በኢትዮጵያ የተመዘገቡትን አይነት የተሻሉ አፈጻጸሞች ለሌሎች ሀገራት መነሳሳትን የሚፈጥሩና ልምድ የሚወሰድባቸው መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
More Stories
ፕሬዚዳንት ፑቲን ጦርነቱን ማቆም ይፈልጋሉ፡- ፕሬዚዳንት ትራምፕ
ጆ ባይደን በካንሰር ህመም መያዛቸው ተነገረ
የፕሬዝዳንቶቹ የስልክ ውይይት