May 2, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

” የፕሬስ ነጻነት ቀን ስናከብር ዜጎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መረጃ እንዳይጭበረበሩ ትክክለኛ መረጃ የሚያገኙበት እሳቤ የሚያጎላበት ቀን ሊሆን ይገባል፡፡”

ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን፤ በሕግ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ ከ100 በላይ የህዝብ ፤የንግድ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንን፤የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፤

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ አማካይነት በየዓመቱ ሚያዝያ 25 ወይም ሜይ 3 የሚከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በአለም ዙሪያ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ ለመገምገም፣ መገናኛ ብዙሃን በነጻነታቸው ላይ ከሚሰነዘረው ጥቃት ለመከላከል እና ህይወታቸውን ላጡ ጋዜጠኞች ክብር ለመስጠት የሚከበር በመሆኑ የመገናኛ ብዙኃንና የፕሬስ ነፃነት አቀንቃኞች ዕለቱን በተለየ ሁኔታ ይመለከቱታል፡፡

ዓለም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) በፍጥነት እየተቀበለች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) “ሰው ሰራሽ አስተውሎት በፕሬስ ነፃነት እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ” የሚለውን ርዕስ የዘንድሮውን የ2025 የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን መሪ ሃሳብ አድርጎ ወስኗል። ይህ ወሳኝ ትኩረት AI ለገለልተኛ ጋዜጠኝነት፣ ለመገናኛ ብዙሃን ዘላቂነት እና ለህዝብ አስተማማኝ መረጃ ተደራሽነት የሚፈጥራቸውን እድሎች እና ስጋቶች ለመፍታት ያለመ ነው።

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር በዓለም ዙሪያ ተከታታይ ዝግጅቶች እና ተግባራት የሚዘጋጁ ሲሆን ይህም ኮንፈረንሶችን፣ ዎርክሾፖችን፣ የፓናል ውይይቶችን እና የሚዲያ ዘመቻዎችን ይጨምራል። እነዚህ ተነሳሽነቶች ጋዜጠኞችን፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ምሁራንን እና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮችን በማሰባሰብ ግንዛቤዎችን እንዲለዋወጡ፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን እንዲካፈሉ እና በ AI ዘመን የፕሬስ ነፃነትን ለመጠበቅ ስትራቴጂዎችን እንዲያዘጋጁ ያደርጋል።

በዚህ ዘመን AI ለፕሬስ ነፃነት እና ለመገናኛ ብዙሃን እጅግ በጣም ብዙ እድሎችን እና ከፍተኛ ተግዳሮቶችን ይዞ መጥቷል። በመሆኑም የዘንድሮውን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሰናከብር የAIን እድል ለመልካም ነገር እንዴት መጠቀም እንደሚቻል እና በተመሳሳይ ጊዜ ለገለልተኛ ጋዜጠኝነት እና አስተማማኝ መረጃ ተደራሽነት ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋዎች እንዴት መቀነስ እንደሚቻል ውይይት ለማድረግ መድረክ ይፈጥራል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች AI የመገናኛ ብዙሃን ገጽታን በሚቀርጽባቸው መንገዶች ላይ ሲወያዩ የሚከተሉትን አጀንዳዎች ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል እንላለን፡፡

በ AI የሚመራ የተሳሳተ መረጃ እና ማጭበርበርን በተመለከተ AI የሐሰት ወይም አሳሳች መረጃዎችን የመፍጠር እና የማሰራጨት አቅም እንዳለው በመገንዘብ ፣ የሀሰት ዜናዎችን የመዋጋት እና በህዝብ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ያለውን እምነት የመጠበቅ ተግዳሮቶችን ላይ መስራት ያስፈልጋል።

ሂደቱ በጋዜጠኝነት ስራዎች እና ክህሎቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በመገምገም AI የጋዜጠኞች የሥራ ዕድሎችን እንዴት ሊጎዳ እንደሚችል እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በ AI በሚመራ ሚዲያ ላይ ለመስራት አዳዲስ ክህሎቶችን እንዴት እንሚያገኙ ማቀድ ያስፈልጋል።

ከዚህ ሌላ በAI የመረጃ ትንተና፣ እውነታን ማረጋገጥ፣ የይዘት ፈጠራ እና የተመልካቾችን ተሳትፎ በሚያሻሽሉ መሳሪያዎች አማካኝነት የጋዜጠኝነት ልምዶችን የማሳደግ አቅምን መገንዘብን የሚጨምር ሲሆን የሥነ ምግባር እሳቤዎች እና ደንቦች መከተል ይገባል፡፡ ይህም ማለት AI በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ በኃላፊነት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ፣ የሰብአዊ መብቶችን በማክበር እና ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን በማስተዋወቅ ረገድ አስፈላጊ የሆኑትን የስነምግባር ማዕቀፎች እና የቁጥጥር ዘዴዎች መወያየት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ያሻል።

የዘንድሮ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ክብረ በዓል ሲከበር የሀገራችን ጋዜጠኞች የዓለማችንን የቴክኖሎጂ እሳቤ ጠንቅቀው በመረዳት ፤ ትክክለኛ መረጃን ለህብረተሰቡ በማድረስ በኩል ያላቸውን የማይተካ ሚና እንዲያጎለብቱ እድል ይፈጥራል፡፡

የሀገራችን መገናኛ ብዙሃን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ የመጡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እድገቶችን በመረዳትና በማጠናከር፣ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ህጐች፣ አሰራሮችና ከቴክኖሎጂው ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ጎጂ የመብት ጥሰት ልምዶች ላይ መወያየት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ምክር ቤታችን ያምናል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሁሌም እንደሚለው ጋዜጠኝነት ይበልጥ ሙያውን ያከበረ ስነ ምግባሩን የጠበቀ፤ ጋዜጠኞች ከስጋትና ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ነፃ ሆነው የሚሰሩበት ምህዳር እንዲኖር እንዲሁም ዜጎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት መረጃ እንዳይጭበረበሩ ትክክለኛ መረጃ የሚያገኙበት እሳቤ የሚያጎላበት ቀን ሆኖ በዓሉ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ሚያዝያ 24 ቀን 2017 አዲስ አበባ፤