
ኢትዮጵያ የብሪክስ ባንክ በሆነው ኒው ደቨሎፕመንት ባንክ አባል ለመሆን እየሰራች ነው :: ኢትዮጵያ የብሪክስ ባንክ በሆነው ኒው ደቨሎፕመንት ባንክ አባል ለመሆን እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።በቅርቡ በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረጉት የተመድ ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀስላሴ ጋር ተገናኝተው በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ተናግረዋል። የፊታችን ሀምሌ ወር ኢትዮጵያ 4ኛውን የፋይናንስ ለልማት ኮንፍረንስ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ገልጸው፤ ለዚሁ ስራ ከመንግስታቱ ድርጅት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ እና ስሎቬኒያ መካከል የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ምክክር መደረጉን ጠቁመዋል። የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ አልዳባቢያ በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝትም ስኬታማ እንደነበር ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡በዚህም የሊቢያው ጠቅላይ ሚኒስትር ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር ሀገራቱ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውንም አንስተዋል።በሩሲያ ሞስኮ ከተማ በተደረገው የብሪክስ አባል ሀገራት ምክክር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ መሳተፉን ገልጸዋል።ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል የሆነችው ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎቷን ለማሳካት መሆኑንም አቶ ነብዩ ተድላ በመግለጫቸው አስረድተዋል።በምክክር መድረኩ የብሪክስ አባል ሀገራት ተሳትፎ መገምገሙንና ለቀጣይ የቡድኑ ስብሰባ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች መነሳታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ የብሪክስ ባንክ በሆነው ኒው ደቨሎፕመንት ባንክ አባል እንድትሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።በስብሰባው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ምክክር መደረጉን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ልዑክ ከአባል ሀገራት ተወካዮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማድረጉን ገልፀዋል።
More Stories
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከዳያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳ ማሰባሰብ ጀመረ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የዘርፍ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2017 በጀት አመት የአስፈፃሚ አካላት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ማህበረሰቡ በከባድ ዝናብ ምክንያት ከሚከሰቱ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።