
የመራጮች ምዝገባ እስከ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡በ6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ቀሪ ምርጫ በሚደረግባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም ድጋሚ ምርጫ በሚደረግባቸው በጅግጅጋ 2 እና መስቃንና ማረቆ ምርጫ ክልሎች ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ምርጫ ለማከናወን ዝግጅቶች እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ለዚህም ከሚያዝያ 21 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ ነው ቦርዱ የገለጸው፡፡ነገር ግን የመራጮች ምዝገባ በወጣበት የጊዜ ሰሌዳ ወቅት ተደራራቢ የሕዝብና የሃይማኖት በዓላት ስለነበሩ፣ የመራጮች ምዝገባ የሚደረግባቸው አንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች በወቅቱ ባለመከፈታቸው ብሎም በምርጫ የሚወዳደሩት የፓለቲካ ፓርቲዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የመራጮች ምዝገባ ቀን እንዲራዘም በመጠየቃቸው የመራጮችን የምዝገባ ቀን እስከ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ማራዘሙን ቦርዱ አስታውቋል፡፡በመሆኑም ምርጫ በሚካሄድባቸው ምርጫ ክልሎች የሚገኙ መራጮች የተሰጠውን የመራጮች የምዝገባ ወቅት በመጠቀም ለምዝገባ ብቁ የሚያደርጉ ማስረጃዎችን በመያዝ በየአካባቢያቸው በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት በመራጭነት መመዝገብ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡
EBC
More Stories
ባለፉት ሦስት ዓመታት ለሰብዓዊ ድጋፍ በሚል የገባ ስንዴ የለም – አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)
በገጠሩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መንግስት የሚዘረጋቸውን የተለያዩ ኢንሸቲቦችን ቀድሞና ፈጥኖ ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር የተሻሉ አፈጻጸሞች መታየታቸው ተገለፀ ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ6 ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ