September 16, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ክልሉ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለፁ ።

ማሻ ፣ የሀምሌ 01፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) በሸካ ዞን የቴፒ አየር ማረፊያ ዳግም ሥራ የማስጀመር እና የቴፒ ቡና ቅምሻ ማዕከል የፈደራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል ።

በምረቃ ፕሮግራም ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልክት ያስተላለፉት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ የሸካ ዞን በጥቅጥቅ ደን የተሸፈነና በውስጡ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት እንዲሁም በክልሉ የቡናና ቅመማ ቅመም ምርቶች በብዛት የሚመረትበት አካባቢ ስለመሆኑ ተናግረዋል ።

በመሆኑም አሁን ላይ የተመረቁ የቴፒ የቡና ቅምሻ ማዕከልና የቴፒ አየር ማረፊያ ዳግም ሥራ መጀመሩ የአካባቢውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማሳለጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው በዞኑ የተመረቁ ፕሮጀክቶች የክልሉን ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ የስራ እንቅሰቃሴዎችን ለማቀላጠፍ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል ።

ክልሉ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የኢፌዲሪ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክቴር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይበልጥ እንዲያድግ የቡና ምርት አንዱና ዋነኛ መሆኑን በመግለፅ በዓመት ከ4መቶ 68 ሺ በላይ ቶን ቡናን በማምረት ወደ 2 ነጥብ 6 ቢልዮን ዶላር ገቢ ኢትዮጵያ አግኝታለች ብለዋል።

አሁን ላይ በሸካ ዞን የተመረቀው የቴፒ ቡና ቅምሻ ማዕከል የአካባቢውን የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ተስፍ ሰጭ በመሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በኢፌዲሪ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ዓለሙ ስሜ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሚቹ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሠረተ ልማት ስራዎችን ለሟሟላት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

ዘጋቢ አስቻለው አየለ