ማሻ ፣ የሰኔ 24፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም፣ በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ፣ የ2016 ዓ.ም የክልሉን አጠቃላይ ሶሾዮ ኢኮኖሚ መረጃ ማጥራት እና የክልሉን የሥነ ህዝብ ምክር ቤት ማቋቋም ላይ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቤቴልሔም ዳንኤል የሥነ ህዝብ ምክር ቤትን ማቋቋም አስፈላጊነትን በመረዳት በክልሉ እየታየ ያለውን ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት ከልማት ዕድገትና ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን በማድረግ ድህነትን ደረጀ በደረጃ በመቀነስ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ወ/ሮ ቤቴልሔም አክለው ሶሾዮ ኢኮኖሚ መረጃ የክልሉ አጠቃላይ ገጽታን የሚገልፅ እና ለሌሎች በርካታ የመንግሥት ውሳኔዎች እና ስራዎች መሠረት በመሆኑ በየጊዜው የሚሰበሰበው የሶሾዮ ኢኮኖሚ መረጃ ተአማኒ እና ወቅታዊ ሊሆን ይገባልም ብለዋል።
በመድረኩ ከሶሾዮ ኢኮኖሚ መረጃዎች አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ክፍተቶች ላይ በመወያየት ችግሮቹን በማረም በቀጣይ 2018 በጀት ዓ.ም የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ በሃላፊነት መስራት እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።
የ2017 በጀት ዓመት እስከአሁን ክልሉ ከተመሰረተ ጀምሮ ተጠንቶ የማያውቀውን የክልሉን የሀብት ግመታ (RGDP) ጥናት ማስጠናት ተጀምሮ የተሻለ ስራ መሰራቱን ወ/ሮ ቤቴልሔም ገልፀዋል።
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ መቱ አኩ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ የክልላችንን አጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፈጣን ዕድገት እና የህዝብን ዘላቂ ልማት ለማምጣት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝና የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ያለ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቢሮው በተለይም ከህዝብ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በሚሰሩ ስራዎች ላይ ተገቢ የሆኑ መረጃዎችን በመያዝ በምክር ቤት ደረጃ እንዲመራ በማድረግ እንዲሁም የሥነ ህዝብ ምክር ቤት መድረኮችን በመፍጠር በየደረጃው ባለው መዋቅር ደረጃ በማቋቋም በዕቅድ እንዲመሩ በማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበትም አቶ መቱ ገልፀዋል፡፡
በምክክር መድረኩ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ መቱ አኩ፣ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቤቴልሔም ዳንኤልን ጨምሮ የክልል ቢሮዎች፣ የዞን፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደር ፕላን ጽ/ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ክልል ኮሚኒኬሽን
More Stories
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከዳያስፖራው ማህበረሰብ አጀንዳ ማሰባሰብ ጀመረ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የዘርፍ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2017 በጀት አመት የአስፈፃሚ አካላት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ማህበረሰቡ በከባድ ዝናብ ምክንያት ከሚከሰቱ አደጋዎች እንዲጠነቀቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።