“በነዳጅ ላይ የተጣለ አዲስ ታክስ የለም” አቶ አህመድ ሺዴ
ማሻ ፣ የሰኔ 24፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በነዳጅ ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያስከትል አዲስ የተጣለ ታክስ የለም አሉ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት እያካሄደ ባለው 41ኛ መደበኛ ስብሰባ በፌዴራል መንግስት የ2018 ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት አድርጓል።
የረቂቅ በጀቱን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት አቶ አህመድ ሺዴ፤ ከዚህ በፊት ምክር ቤቱ በነዳጅ ላይ ከጣለው ታክስ ውጪ ሌላ አዲስ ታክስ የለም ነው ያሉት።
ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት ይህንን የነዳጅ ታክስ ያጸደቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሙሉ በሙሉ ወደ መሰብሰብ አለመገባቱን እና ከጸደቀው የታክስ መጠን ውስጥ ግማሹ በነዳጅ ድርጅት በኩል ሲሰበሰብ እንደነበር አስታውሰዋል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ይህ የሚሰበሰበው ታክስም መልሶ ለድጎማ እንዲውል መደረጉን አብራርተው፤ አሁን ላይ የአሰራር ለውጥ መደረጉን ተናግረዋል።
አሰራሩ በታክስ አሰባሰብ ዙሪያ ያለውን የፋይናንስ ግልጸኝነት የሚያረጋግጥ የሪፎርሙ አካል መሆኑን ገልጸው፤ በጉሙሩክ ኮሚሽን በኩል ተሰብስቦ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ቋት እንዲገባ ከተደረገ በኋላ መልሶ ለድጎማ እንደሚውል አስረድተዋል።
በመሆኑም የአሰራር ማስተካከያው በቀጥታ በነዳጅ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲፈጠር የሚያደርግ ውሳኔ አለመሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
በነዳጅ ላይ ከተጣለው ታክስ ውስጥ ምን ያልሉ እንደሚሰበሰብ የሚመለከታቸው አካላት ወቅታዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ ውሳኔ እንደሚሰጡበት ጠቁመዋል።
የሕብረተሰቡን ጫና በመገንዘብ ከፍተኛው የማሕበራዊ ድጎማ በዘንድሮ የበጀት ዓመት ተግባራዊ መደረጉን እና በሚቀጥለው ዓመትም በተወሰነ ደረጃ ይቀጥላል ብለዋል።
በዚህም የአፈር ማዳበሪያ ላይ የሚደረገው ድጎማ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተው፤ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራ አቋም መያዙን ነው ያመለከቱት።
ፋና
More Stories
ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን በላይ የቡና ምርት አግኝታለች
ለሀገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ቡና እንደ ወረዳ ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ ሽፋን መኖሩን በሸካ ዞን የየኪ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።
ምክር ቤቱ የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ በዝርዝር እየተወያየ ነው