ማሻ ፣ የግንቦት 14፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) ቶትነሃም ማንችስተር ዩናይትድን 1 ለ 0 በማሸነፍ የዘንድሮውን የአውሮፓ ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ የቀጣዩ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊነቱም አረጋግጧል።
ሁለቱ ክለቦች ዘንድሮ በእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ በደረጃ ግርጌ ላይ መቀመጣቸውን ተከትሎ በቀጣዩ የአውሮፓ ቻምፒንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን የሚያስችላቸው ቁመና ላይ አልነበሩም። ይህንን ትልቅ የአውሮፓ ውድድር ለመቀላቀል ብቸኛው መንገድ አውሮፓ ሊግ ዋንጫን ማሸነፍ ነበር። እናም ሁለቱም ይህንን ውድድር ከዋንጫ በዘለለ ይፈልጉት ነበር።
ከታሪክ አንጻር ሲታይ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ቶተንሃም 2 ጊዜ ማንሳት የቻለ ሲሆን ማንችስተር ዩናይትድ አንድ ጊዜ ነው አሸናፊ የሆነው። ሆኖም ቶትነሃም ዘንድሮ ማሸነፉን ተከትሎ የአውሮፓ ሊግ ዋንጫ አሸናፊነት ታሪኩብ ወደሶስት ከፍ አድርጓል።
ቶተንሃም ለ17 አመታት የዘለቀው የዋንጫ ጥሙን ለማራስ አቅዶ ወደሜዳ በመግባት ህልሙን ማሳካት ችሏል። ማንቸስተር ዩናይትድ የአውሮፓ ሊግን ያሸነፈው እአአ በ2017 በጆዜ ሞሪንሆ እየተመራ አያክስን አሸንፎ ነው።
ቶተንሃም በዚህ የውድድር ዓመት ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ያደረጋቸዉን አራቱንም ጨዋታዎች አሸንፏል።
የሁለቱ ክለቦች የፍፃሜ ጨዋታ በስፔን የባስክ ግዛት በሚገኘው እና 53 ሺህ 289 ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው የሳን ማሜስ ስታዲየም ነው የተደረገው።
በዩሮፓ ሊጉ ግማሽ ፍፃሜ ማንቸስተር ዩናይትድ የሜዳውን ባለቤት አትሌቲክ ቢልባኦን እንዲሁም ቶትንሃም ቦዶ ግሊምትን በደርሶ መልስ በማሸነፍ ለፍፃሜ መድረሳቸው ይታወሳል።
የማንችስተር ዩናይትዱ ታሪካዊ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን የምሽቱን የፍፃሜ ጨዋታ ታድመዋል።
በፕሪሚዬር ሊጉ በተመዘገበው ደካማ ውጤት የተሰበረውን የደጋፊ ልብ መጠገን፣ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት የምድብ አባት በመሆን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በቀጥታ መሳተፍ፣ በሚገኘው የገንዘብ ገቢ ዕዳን መክፈል እና ተጫዋች በማስፈረም ቡድንን ማጠናከር የሚያስችል እና ተጫዋችን ለማስፈረም በድርድር ወቅት በሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ መሆንን ማውሳት እንደማማለያ የሚጠቅም በመሆኑ በአጭሩ የዩሮፓ ሊጉ ሻምፒዮን መሆን ፋይዳው የጎላ ነው።
ጨዋታውን የመሩት ጀርመናዊው ዋና ዳኛ ፍሊክስ ዝዌይር ናቸው።
More Stories
54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠናቀቀ
ማንቼስተር ዩናይትድና ቶተንሃም ለዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ አለፉ
ቼልሲ እና ሪያል ቤቲስ ለዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ፍጻሜ አለፉ