May 15, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አመርቂ ስኬት አስመዝግቧል – ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

ማሻ ፣ የግንቦት 06፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም) የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ስኬት ማስመዝገቡን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል።

በፎረሙ ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ የባንክ የስራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብና የልማት አጋር ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፥ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የሚፈለገውን ያህል ዕድገት ሳያስመዘግብ መቆየቱን አውስተዋል።

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የነበሩ መሰናክሎችን ለማለፍም አካታችና ዘመኑን የዋጀ ሥርዓት የሚፈጥር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በተደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለማሸጋገር ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም ለዘርፉ አንገብጋቢ ችግሮች ምላሽና መፍትሔ አመላካች ምክረ ሃሳቦችን በመስጠት የግሉን ዘርፍ ለማነቃቃት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ ድጋፍና ዕውቅና ማግኘቱን ጠቁመዋል።

ደሬቴድ