የአራዳ ፓርክ የፒያሳን ገጽታ የቀየረ እና የነዋሪዎችን ሰብአዊ ክብር ያስቀደመ ፕሮጀክት ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
በትናንትናው ዕለት አዲሱ የአራዳ ፓርክ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
ከንቲባዋ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር እንዳሉ፥ ፕሮጀክቱ የከተማዋን መልክ ከመቀየር ባለፈ ለዘመናት ተረስተው የነበሩ ዜጎችን ሰብአዊ ክብር የመለሰ ነው።
ይህ ስራ ከመከናወኑ በፊት በፒያሳ አካባቢ የነበረው ሁኔታ የኢትዮጵያዊያንን አሻራ የማይገልጽ፣ አስከፊ ድህነት የሚታይበት፣ ነዋሪዎች በመጸዳጃ ቤት እጦት፣ በጠባብና በማይመቹ ቤቶች ውስጥ ለጎስቋላ ህይወት ተዳርገው የቆዩበት መሆኑን አስታውሰዋል።
በተለይም በወንዝ ዳርቻ የነበረው ብክለት ለነዋሪዎች ጤና ጠንቅ ከመሆን ባሻገር የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሽ እና የወንጀል መገለጫ ሆኖ እንደነበር አንስተው፥ ልማቱ የነዋሪዎችን ሰብአዊ ክብር ለማስመለስ የተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የልማቱ ዋና መነሻ ሰው መሆኑን በማንሳት መንግሥት ለነዋሪዎቹ ቅድሚያ በመስጠት፣ በላፍቶ 2 ሺህ አካባቢ ለሰው ልጅ ክብር የሚመጥኑ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ማስረከቡን ጠቁመዋል።
የአራዳ ፓርክ ግንባታም ለማንም በተናጠል ሳይሆን ለሕዝብ የጋራ ጥቅም ታስቦ የተሰራና አረጋውያንን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችንና ህጻናትን ያካተተ ሁለንተናዊ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።
የአራዳ ፓርክ በተፈጥሮ ውበትና በዘመናዊ ማሳለጫዎች የተሟላና ሰፊ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ አበቦች፣ ዛፎችና አእምሮን የሚያድሱ የውሃ ፏፏቴዎችን ያካተተ መሆኑን ገልጸው፥ በውስጡ ከ131 በላይ ሱቆች፣ የስጦታ እቃ መሸጫዎች፣ የአርት ጋለሪ ይዟል ብለዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባ የስፖርት አሬና እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ለተለያዩ ኩነቶች ማካሄጃነት የሚያገለግሉ ስምንት አዳራሾች፣ በፓርኩ ግራና ቀኝ እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ፕላዛዎች እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
እንዲሁም የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ፣ 5 ኪሎ ሜትር የሳይክል እና 6 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ መዘጋጀቱ የገለጹት ከንቲባዋ፥ ለህጻናት ልዩ ትኩረት በመስጠት 5 የመጫወቻ ስፍራዎች መገንባቱን እና ከነዚህም ውስጥ አራቱ በነጻ አገልግሎት እንደሚሰጡ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን ክብር ከፍ አድርጎ የሚገልጽ 100 ሜትር ርዝመት ያለው የብሔራዊ ባንዲራ መስቀያም በዚሁ ፓርክ ውስጥ መተከሉን ነው የገለጹት።
ቀደም ሲል ለጤና ጠንቅና ለወንጀል መናኸሪያ የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎች ዛሬ ለቱሪስት መስህብና ለስራ እድል ፈጠራ መዋላቸውን ገልጸው፥ ለዚህ ታላቅ ስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ከፍተኛ አመራሮችን አመስግነዋል።
በተጨማሪም ሕዝቡ ይህንን ውብ ስፍራ መጥቶ እንዲጎበኝና እንዲጠቀምበት ጥሪ አቅርበዋል።
More Stories
አሜሪካ ከኢራን ጋር ባደረገችው ጦርነት 25 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አጣች
መሬት በድንገት መሽከርከር ብታቆም ምን ሊፈጠር ይችላል?
ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው